የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው የቆዩ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ተመለሱ።
በምስራቅ ደንቢያና በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ሲቀሳቀሱ የነበሩ የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው የቆዩ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ትጥቃቸውን ለመንግስት አስረክበዋል።
የጎንደር 44ቱ ክፍለ ጦር አንዳርጌ ብርጌድ አዛዥ አስር አለቃ አስናቀ ሽጉጥ በሰጠው አስተያየት መንግስት ያደረገልንን የሰላም ጥሪ ተቀብለናል ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሰናል ሲል አስተያየቱን ገልፆል።
መጀመሪያ የወጣነው የአማራ ህዝብ እየተፈናቀለ ነው በሚል ሃሳብ ወደ ጫካ ገብተናል ያለው አስተያየት ሰጭው አሁን ላይ ግን የአማራን ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ ለችግር ማጋለጥ ሆኖ ስላገኘነውና የውጭ ወራሪን ለመከላከል በማሰብ መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተከትለናል ብለዋል።
የጎንደር 44ቱ ክፍለ ጦር አንዳርጌ ብርጌድ ሻለቃ መብራት ወርቁ ደግሞ እስካሁን በዱር በገደሉ ስንገላታ ቆይተናል።
አሁን ላይ የመንግስትን የሰላም አማራጭ ተከትለን ህዝባችን ለማገልገል ተዘጋጆተናል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሌላው አስተያየት ሰጭ ሀብታሙ አባይ ደግሞ እስካሁን ስንሄድበት የነበረውን የተሳሳተ መንገድ መሆኑን በመረዳት የሰላም አማራጩን ተቀብለናል ብለዋል።
አሁን የህዝቡን ችግር ተረድተናል ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ ሌሎችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጥሪያችን እናስተላልፋለን ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ ደግሞ በምስራቅ ደንቢያና በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ሲቀሳቀሱ የነበሩ 15 ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላም እጃቸውን ለፀጥታ ሃይሉ መስጠታቸውን ገልፀዋል።
ታጣቂዎቹ ለፀጥታ ሃይሉ በሰላም እጃቸውን ሲሰጡ ሁለት የሬዲዮ መገናኛዎችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
በከተማችን አሁን ላይ የፀጥታ ሃይሉና ህብረተሰቡ በቅንጅት መስራት በመቻሉ ከተማው አንፃራዊ ሰላም ላይ መሆኑን ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ነው።





