“ትኩረትን ከሚሰርቁ፣ ኀይልን ከሚበትኑ፣ ለጠላት ተጋላጭ ከሚያደርጉ እና ሰላምን ከሚያውኩ አሰራሮች በመራቅ ለሙያችን ተገዢ በመሆን ህዝብን ማገልገል ይገባል!” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለባህርዳር እና ጎንደር ቀጠና ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ከህዳር 10/2018 ዓ/ም እስከ ህዳር 15/2018 ዓ/ም ድረስ ሲሰጥ የቆየው የጅኦ ስትራቴጂካዊ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በስልጠናው ማጠቃለያ ተገኝተው የቀጣይ ተግባራት እና አቅጣጫዎችን አስመልክቶ መመሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ በውስጣችን ያሉ ከፋፋይ እና ኃላፊነትን የሚያጎድፉ አሰራሮችን በማስወገድ እንዲሁም ሙያዊ ኃላፊነትንና ማዕረግን ያከበረ አሰራርን በመተግበር ህዝባችን ከገባበት የሰላም እጦት ማላቀቅ ወቅታዊ የሰራዊታችን የአርበኝነት መገለጫ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ውስጣዊ ባንዳዎችን ብቻም ሳይሆን ውጫዊ ባዳዎችን ማጽዳት ያስፈልጋል ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በጠላት የውሸት ሴራ ሳንጠለፍ በያዝነው አላማ እና ራዕይ መጽናት እንደማገባ አብራርተዋል።
“ትኩረትን ከሚሰርቁ፣ ኀይልን ከሚበትኑ፣ ለጠላት ተጋላጭ ከሚያደርጉ እና ሰላምን ከሚያውኩ አሰራሮች በመራቅ ለሙያችን ተገዢ በመሆን ህዝብን ማገልገል ይገባል!” ሳሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አክለውም የፖሊስ አመራሩ በጸጥታና በልማት ስራዎች ላይ አርበኝነቱን የሚያሳይበት ወርቃማ ጊዜ አሁን ነው።
ተቋማዊ ፍቅርና የህዝብ አገልጋይነት ስሜትን መላበስ ለነገ የማይተው ተግባራችን ነው ሲሉ አክለው አብራርተዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው በተሰራው የሪፎርም ስራ ከተቋም እድገት ባሻገር የፖሊስ ሰራዊቱን ተስፋና የመስራት ሞራል ያሳደገ ነው ብለዋል።
የሰው ኃይል አያያዝን ማዳበር እንዲሁም የአቤቱታ አቀባበል እና የችግር አፈታት ስርዓትን ማስተካከል ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል።
የክልሉን ህዝብ ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ቆራጥና ጠንካራ የሆነ ሰራዊትን በመፍጠር የተጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ በመረጃ አያያዝና በወንጀል ምርመራ ስራም ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ አሰራርን መከተል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የጎንደር ቀጠና ስልጠናን የመሩት ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው አሁን ላይ በክልላችን ላለው አንጻራዊ ሰላም መደበኛና አድማ መከላከል ፖሊሳችን ከጀግናው የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ቀላል የማይባል ዋጋ መክፈሉን አንስተዋል።
እንደ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ገለጻ በሰራነው ስራ ሳንኩራራ በቀጣይ የላቀ ግዳጅን በመወጣት የጠላትን እንቅስቃሴ በማክሸፍ እና የተሟላ ሰላም የማስፈን ተልዕኮን በብቃት መወጣት አለብን ብለዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለፖሊስ ተባባሪ ሊሆን ይገባል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ከፖሊስ ጋር በትብብር የማይሰራ ግለሰብ፣ ማህበረሰብ እና ድርጅት ሊኖር አይገባም ሲሉ አብራርተዋል ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው ሰላም፣ የሀገር ፍቅር እና ፖሊስ የማይነጣጠሉ ናቸው። ስለሆነም ሀገራችን እየጠየቀች ያለችው የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊ እና ፍትሃዊ በመሆኑ የፖሊስ ሰራዊታችንም በአጽንኦት የሚያው ተግባር ነው ብለዋል።
የባህር በር ጥያቄ የሀገርን ክብር ከማጎናጸፉም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ ነው የሚሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ሀገራችን ለዓመታት ተዘግቶባት የነበረው የባህር በር ጥያቄ መልስ የሚያገኝበት ትክክለኛ ጊዜ አሁን መሆኑን አንስተዋል።
ሰልጣኝ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት በባህርዳር እና በጎንደር ከተማዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን እና ታሪካዊ ስፍራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በስልጠናው እና በጉብኝት ፕሮግራሙ ደስ መሰኘታቸውን ተናግረው በአስቸጋሪ ጊዜ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች እንዲጠናከሩ እና የተሟላ ሰላም እንዲረጋገጥ ጓዳዊ ትስስራችን በማጠናከር ለምናደርገው ወንጀልን የመከላከል ተግባር መነሳሳትን ፈጥሮልናል ብለዋል።
የወንጀል መከላከል ስራዎችን በማጠናከር የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እንድንሰራ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት የስልጠና ተሳታፊ ፖሊሶች።
ቆራጥ፣ አርቆ አሳቢና ግንባር ቀደም የሆነ መሪ መሆን ያስፈልጋል ያሉት ሰልጣኝ ፖሊሶች የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በውል ተገንዝቦ ለማህበረሰባችን ሰላም መስፈን እና ለህግ የበላይነት መከበር በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።
ስልጠናውን ወደ ተግባር በመቀየርና ለአባሉ በማስረዳት የጋራ ሰላማችንን በጋራ ለመጠበቅና ለሚፈጠሩ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማበጀት በጋራ የምንቆምበት አሰራርን መከተል ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።
በመጨረሻም ሰልጣኞች ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት እና ቃላቸውን በማደስ ስልጠናው ተጠናቋል።
ስልጠናው በሌሎች ቀጠናዎች እና በተዋረድ ላሉ የፖሊስ ሰራዊቱ አመራሮች እና አባላት እንደሚሰጥ የወጣው መርሀ-ግብር ያመለክታል።

























