በተማሪ ሊዛ ደሳለኝ ግድያ የተጠረጠረው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
ተማሪ ሊዛ ደሳለኝ መስከረም 28/2018 ዓ.ም ምሽት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገላ መገኘቷ የደሴ ከተማን ህዝብ ያስቆጣ እና ለወጣቷ ፍትህ እንድታገኝ የተጠየቀበት ነበር።
የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በተማሪ ሊዛ ደሳለኝ ሞት ማዘኑን ገልጾ በወንጀሉ የተጠርጣሪውን ግለሰብ በመያዝ ለፍትህ እንደሚያቀርብ ቃል ገብቶ የነበረ ሲሆን ቃሉን በተግባር ፈጽሟል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጥላሁን ታደሰ የተማሪ ሊዛ ግድያ አሳዛኝ እና ውስብስብ በመሆኑ የምርመራ ቡድን በማዋቀር እና ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት ተጠርጣሪው ህዳር 2/2018 ዓ/ም በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።
ከአንድ ወር በላይ በፈጀው የምርመራ እና የክትትል ሂደት ከማህበረሰቡ ያገኘው ድጋፍ እንዳበረታውና አቅም እንደሆነው የፖሊስ መምሪያ አዛዡ ገልጸዋል።
በመምሪያው የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ተሾመ ተስፋዬ በበኩላቸው ምርመራው ውስብስብ እና አስቸጋሪ ቢሆንም በቀጣይ የሚገኙ ውጤቶችን ለማህበረሰቡ ይፋ እንደሚያደረጉ አስታውቀዋል።
ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅሮ ተጠርጣሪውን ለህግ በማቅረብ ተገቢውን ፍትህ ለማሰጠት እንደሚሰራም የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አብራርቷል።

