የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለፖሊስ አባላት እና መሪዎች እውቅና ሰጠ።

የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለፖሊስ አባላት እና መሪዎች እውቅና ሰጠ።

የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የላቀ አፈጻጻም ላከናወኑ የፖሊስ አባላት እና አመራሮች የእውቅና እና የማበረታቻ መርሐ ግብር አካሄዷል።

ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ላለፉት 33 ዓመታት ከ130 ሺህ በላይ የፖሊስ አባላትን በተለያየ ሙያ አሰልጥኖ ወደ ስራ በማሰማራት ለህግ የበላይነት መከበር የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ አንጋፋ የስልጠና እና የምርምር ተቋም ነው ብለዋል።

ላሳዩት የላቀ አፈፃፀም እንዲበረታቱ የተፈቀደላቸው የፖሊስ አባላት እና አመራሮች በቀጣይ የበለጠ የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ አደራ ጭምር ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከሐምሌ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደረጃ እንዲያድግ መደረጉ ለተቋሙ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሯል ብለዋል።

በተቋሙ አዳዲስ የስልጠና መርሐ ግብሮችን በመቅረጽ ዋና የጥናት እና ምርምር ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት አስገንዝበዋል።

የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ የሚገኝ ተቋም ነው ያሉት የደብረ ማርቆስ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ናቸው።

ተቋሙ ዓለም አቀፋዊ ይዘትን ተላብሶ የማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ልምድ የሚወሰድበት እንዲሆን በጋራ መስራት አለብን ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሀኑ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በስነ-ምግባር የተገነቡ እና ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉ የፖሊስ አባላትን ለማፍራት የጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ዘመኑን የሚመጥን አሰራር በመዘርጋት ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ሕዝቡ ከገጠመው የጸጥታ ችግር ማሻገር የሚችል ፖሊሳዊ ተቋም እንዲሆን በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የአማራ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በእውቀትእና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ብቁ የጸጥታ ኀይል በመገንባት እየተጋ ያለ ተቋም ነው ያሉት ደግሞ በዕውቅና ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ናቸው።

የፖሊስ አባላቱ ያገኙትን ማዕረግ ወደ ላቀ ተግባር በመቀየር እና ተልዕኮን በላቀ ቁርጠኝነት በመወጣት በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ መቋጫ እንዲያገኝ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአሳዩት አፈፃፀም እውቅና እና ማበረታቻ የተሰጣቸው የፖሊስ አባላት እና አመራሮች ያገኙት ማዕረግ እድገት እና እውቅና የተሰጣቸውን ኀላፊነት አጉልተው በመወጣት ማኅበረሰቡ እያጋጠሙት ካሉ ችግሮች እፎይታ እንዲያገኝ በላቀ ደረጃ እንድንሰራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ተቋሙ በ1985 ዓ.ም ከማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተነስቶ አሁን ለደረሰበት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደረጃ እንዲደርስ ጉልህ ድርሻ ላበረከቱ ተቋማት እና የስራ ኀላፊዎች ምስጋና ቀርቧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top