በማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ ሀሳብና አሰራር ዙሪያ የስልጠና ተሰጠ።

በማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ ሀሳብና አሰራር ዙሪያ የስልጠና ተሰጠ።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ ለ4ኛ፣ 8ኛ እና 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ አመራሮች እና አባላት የማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ ሀሳብ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል።

በዕለቱ ተገኝተው ስልጠናውን የሰጡት በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ያሬድ አበበ እንደተናገሩት ማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ ሀሳብ ወንጀል ከመከላከል ባሻገር ማህበረሰቡን የጸጥታው ባለቤት ያደረገ፣ የፖሊስን እና የማህበረሰቡን ግንኙነት የሚያጠናክር አሰራር ነው ብለዋል።

ወንጀልን ለመከላከልና ሰላምን ለማስጠበቅ ከጸጥታ አካላት በበለጠ የማህበረሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ኮማንደር ያሬድ አበበ የፖሊስ አጋዥ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና ውጤታማ የወንጀል መከላከል ስራ ለመስራት ጽንሰ ሀሳቡ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

የአሰራሩን ጥቅም እና አዋጭነት በማስረዳት ማህበረሰቡን የጸጥታ ስራው ባለቤት በማድረግ የስጋት ቦታዎችን የተጠናከረ ጥበቃ እና ቅኝት በማድረግ የነዋሪውን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተቀዛቀዘውን የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት አሰራር ዳግም ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስ የፖሊስ ሰራዊቱ ግንባር ቀደም ኃላፊነት እንዳለበት ኮማንደር ያሬድ አበበ አክለው አብራርተዋል።

ኮማንደር ንብረቱ ሞላ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ ዓቀፍ ወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች መረጃና ማስረጃ ለማግኘት ማህበረሰቡን ያሳተፈ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ኮማንደር ንብረቱ ገለጻ የማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ አገልግሎት አሰራር በፖሊስ እና በማህበረሰቡ መካከል መተማመን የሚያጎለብት አሰራር በመሆኑ የተሰጠውን የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።

ስልጠናውን የወሰዱ አመራርና አባላትም የተሰጣቸው የስራ ላይ ስልጠና ለቀጣይ ስራቸው አጋዥ እንደሆነና የተሻለ ልምድ እንዳገኙ በመግለጽ ለቀጣይ አካታች የሆነ የወንጀል መከላከል ስራን ለመስራት ግብዓት እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top