የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት መገንባት ወሳኝ ነው።
የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ እና በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የፍትሕ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር በትብብር መድረኩ በትኩረት መስክ ተይዞ እየተሠራበት ነው ብለዋል።
ጥራት ያለው የፍትሕ አገልግሎት ለመሥጠት የፍትሕ ዘርፉ መሪዎች እና ባለሙያዎችን በሥነ ምግባር እና በሙያ ክህሎት አቅማቸውን ማሣደግ ይገባል ብለዋል።
የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥም ሌላኛው በትኩረት መስክ የተያዘ ጉዳይ እንደኾነ ገልጸዋል። የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት መገንባት ወሳኝ መኾኑንም ነው ያመላከቱት። ለዚህም በሰው ኃይል ግንባታ በኩል አቅደን ሰፊ ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል።
የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ተቋማት የተሠጣቸው ተልዕኮ የሚተሳሰር መኾኑን አንስተዋል። የትብብር መድረኩ በመገፋፋት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በመሙላት ውጤታማ የፍትሕ አገልግሎት ለመሥጠት ያግዛል ነው ያሉት። ለፍትሕ ፈላጊው ማኅበረሰብም የተሻለ አገልግሎት ለመሥጠት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በፍትሕ ሥርዓቱ የሚስተዋለውን የመገፋፋት ችግር እንደሚያስቀር ገልጸዋል።
በተለይም በባለሙያዎች በኩል የሚስተዋለውን የሥነ ምግባር ችግር በጋራ ለማስተካከል እንደሚያስችል ነው የገለጹት።
ጥራት ያለው የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ሥራ ለማከናወን አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል። ለሕግ የበላይነት መከበር በእነዚህ ተቋማት የሚወሰን በመኾኑ የክልሉን የሰላም እና ደኅንነት ለማሻሽል ያግዛል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዓባይነህ በላይ በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የፍትሕ ተቋማት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመገፋፋት ወጥቶ በቅንጅት ለመሥራት ትብብሩ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በፍርድ ሂደት ወቅት ያጋጥም የነበረውን የፍትሕ መጓተት እንደሚያስቀርም ጠቁመዋል። ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በሥነ ምግባር ታንጸው እና ሕግን አውቀው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።
ጥምረቱ በተጀመረው መንገድ የሚቀጥል ከኾነ በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ በኩል ለውጥ እንደሚያመጣ አስተያየት መስጠታቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አስነብቧል።






