ለህገ-ወጥ ቡድኑ ሊደርስ የነበረ ጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ።
መነሻውን ከሱዳን በማድረግ ለህገ-ወጥ ቡድኑ ሊደርስ የነበረ ጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ኮማንደር ምስጋናው ካሴ የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ተናግረዋል።
በ4 ሞተር ብስክሌት ከሱዳን ተጭኖ የተነሳው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ በቋራ ወረዳ ምርት ገለጎ ቀበሌ አድርጎ ለጠላት ሊደርስ የነበረ መሆኑን ነው የፖሊስ አዛዡ አክለው የገለጹት።
የጸጥታ ኃይሉ ባደረገው ብርቱ ጥረት እና ክትትል በቋራ ወረዳ ነብስ ገበያ ቁጥር 4 ልዩ ቦታው ተሾመ እርሾ ላይ መያዝ ተችሏል ሲሉ ነው ኮማንደር ምስጋናው ካሴ የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ያስታወቁት።
እንደ ኮማንደር ምስጋናው ካሴ ገለጻ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ ተጭኖበት የነበረው 4 ሞተር ብስክሌት፣ 01 ክላሽ ጠመንጃ፣ 10 የክላሸ ካዝና፣ 566 የዲሽቃ ጥይት፣ 8260 የብሬን ጥይት፣ 4779 የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር ውሏል ነው ያሉት።
ህብረተሰቡ መሰል ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ለጸጥታ ኃይሉ መረጃ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ኮማንደር ምስጋናው ካሴ የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ መልዕክት አስተላልፈዋል።




