ለጸጥታ አካላት በሰብዓዊ መብት አያያዝና በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ።

ለጸጥታ አካላት በሰብዓዊ መብት አያያዝና በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ።

UNDP PEACE SUPPORT FACILITY ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና የክልሉ ሚሊሻ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ-ሀሳብ ላይ ያተኮረውን ስልጠና የሰጡት ኮማንደር ያሬድ አበበ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዋና መምሪያ ኃላፊ እነደገለጹት የጸጥታ ኃይሉን ከማኅበረሰቡ ፍላጎትና እምነት ጋር የተሳሰረ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ-ሀሳብ ስልጠና በጸጥታ አካላት እና በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን የመተማመን ድልድይ ለመገንባት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ወንጀልን ለመከላከልና የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የኅብረተሰቡን ተሳትፎና ባለቤትነት ማሳደግ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ነው ያሉት የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዋና መምሪያ ኃላፊው።

የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ-ሀሳብ የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ናቸው።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰብዓዊ መብት መከበር እና የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አሠራር መርሆዎች በፖሊስ ሰራዊቱ እና በጸጥታው መዋቅር ውስጥ ሥር እንዲሰዱ ለማድረግ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ አስታውቀዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ሀሳባቸውን የገለጹት ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው ህዝብ የጸጥታው ባለቤት መሆን አለበት ብለዋል።

እንደ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ገለጻ የጸጥታ ስራን በምናከናውንበት ወቅት የዜጎችን ሰብዓዊ መብትን ማክበር የሕግ ማስከበር ሥራችን መሠረት መሆን አለበት ብለዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ-ሀሳብ ስልጠና የፖሊስና የጸጥታ ተቋማት ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዴት ማጠናከር እንደሚችሉ፣ በወንጀል መከላከል ሥራ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ እንዴት ማሳደግ እንደሚገባ፣ እንዲሁም በጋራ በመሥራት የዘላቂ ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top