“ላብ ደምን ያድናል”
የአማራ ክልል ፖሊስ የ34ኛ ዙር ምልምል ፖሊስ ሰልጣኞች በብር ሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እየተሰጠ ይገኛል።
በብር ሸለቆ ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ፣ ላብ ዝም ብሎ ፈሶ የሚቀር አይደለም፤ የሀገር ፍቅር ነጸብራቅ ነው። እዚህ ቦታ ላይ፣ የጀግንነት ታሪክ በየጠብታው ይጻፋል።
የማዕከሉን የስልጠና ሂደት ተዘዋውረን ስንመለከት፣ የሰልጣኞች እና የአሰልጣኞቹ ላብ ሲንቆረቆር አየን። ከሞቃታማው የአየር ጠባይ ጋር ተዳምሮ፣ የስልጠናው ክብደት የማይቋረጥ ላብን አስከትሏል። ነገር ግን፣ ይህ ላብ የድካም ምልክት ሳይሆን፣ የቁርጠኝነት ማሳያ ነው። “ላብ ደምን ያድናል” የሚለው መርህ፣ እዚህ ቦታ ላይ በግልጽ ይታያል።
እያንዳንዱ የስልጠና ወረዳ፣ በጀግኖች ላብ የታነጸ ነው። የሀገር ፍቅር እሳት በሰልጣኞች ልብ ውስጥ ሲቀጣጠል፣ ላባቸው ይወርዳል ይፈሳል። ይህ ላብ፣ ለሀገር ፍቅር የሚከፈል ውድ ዋጋ ነው።
የብር ሸለቆ መሰረታዊ የውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሰራዊታችን አለማቀፍ አምባሳደርነቱን የሚያረጋግጥበት፣ ጠንካራ መሪ መኮንኖች እና የሀገራችን ድንበር የሚጠቡቁ ወታደሮች የሚፈጠሩበት ቦታ ነው። እዚህ ቦታ ላይ መሰረታዊ ስልጠናዎች ይጀመራሉ። ሁላችንም፣ ለሀገራችን ደህንነትና ለአለም ሰላም ስንል፣ ላባችንን በደስታ እናፈሳለን።
የምናፈሰው ላብ ስንታጠበው እንደሚጠፋ እናስባለን። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ የላብ ጠብታ የሀገር ፍቅር ማሳያ ነው።
እያንዳንዱ የላብ ጠብታ፣ ለሀገር ክብርና ነጻነት የሚከፈል ውድ ዋጋ ነው። እነዚህ ጠብታዎች፣ በግዳጅ ቀጠና ላይ ሲፈሱ፣ የጀግንነትን ታሪክ ይጽፋሉ። ለትውልድ የሚተላለፍ የጀግንነት ማስታወሻም ይሆናሉ።
ተራራው የማይገዳቸው፣ ሀሩር የማይረታቸው የአማራ ክልል ፖሊስ የ34ኛ ዙር ምልምል ፖሊስ ሰልጣኝ ትንታጎች ናቸው።
በሚንቀለቀለው የሀሩሩ ሙቀት ሳቢያ በመላው የሰውነት ቆዳ ቀዳዳዎች ላብ ያለማቋረጥ ይፈሳል።
መልክዓ-ምድሩ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ቅሪት
በሆኑ ቋጥኞችና የተለያየ መጠን ባላቸው ድንጋዮች የተሞላ ነው። ታዲያ ድንጋዮቹ ያለምህረት ቃጠሎዋን የምትለቀውን የጸሃይ ግለት እየመጠጡ መልሰው ይተፉታልና ፀሐይዋ ከላይ ብቻ ሳይሆን ከታችም ያለች አስመስሏታል።
መቆምም መቀመጥም በሚጨንቅበት ውሃ እየተጠጣ ውሃ በሚጠማበት በዚህ ስፍራ አንድ ለተለያዩ ግልጋሎቶች ሲውል የነበረ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ይገኛል። ብር ሸለቆ መሰረታዊ የውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት።
በዚህ ማሰልጠኛ ‘ቆይ ፀሐይ ትቀዝቅዝ’ የሚባል ነገር የለም። በአንጻሩ ሀሩሩ ክፉኛ በሚንቀለቀልበት የሙቀት ሰዓት ላይ ሁሉም የስልጠና ወረዳዎች በሰልጣኝ እና አሰልጣኝ ትንታጎች ተሞልተዋል።
የሳንጃ ውግ፣ ስልት፣ ተኩስ፣ መሰናክል ብቻ በሁሉም ወረዳዎች “የላብ ደምን ያድናል” መርህን ከላብ ባለፈ ትጋት እንደ ተርብ በየወረዳቸው በአስደማሚ ፅናት ሲሰለጥኑ ሲታይ ይህ ሁሉ ‘ስለ ኢትዮጵያ’ ነውና በትንታጎቹ የሚያስመካ አንዳች ስሜት የሰራ አካልን ይቆጣጠራል።
እኛም የትንታጎቹን አስደናቂ ቅልጥፍናና ወታደራዊ ብቃትን የሚያስመነድግ የአሰለጣጠን ሂደት በካሜራችን ስናስቀር፣ ትንታጎቹን ስናናግር ቆይተን ትንሿን ኢትዮጵያ በእዚህ ማሰልጠኛ ውስጥ ደምቃ አገኘናት።

















