“የአማራ ክልል ፖሊስ የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ ቀን ከሌት በትጋት መስራት ይጠበቅበታል።” ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

“የአማራ ክልል ፖሊስ የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ ቀን ከሌት በትጋት መስራት ይጠበቅበታል።” ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጀብድ ለፈጸሙ እና የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፖሊስ አመራሮ እና አባላት የእውቅና እና ሽልማት መርሐ-ግብር አካሂዷል።

በፕሮግራሙ ተገኝተው የስራ መመሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ከዘረኝነት፣ ጎጠኝገት እና ከሌብነት የጸዳ የፖሊስ ሰራዊት በመገንባት የአማራን ህዝብ ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ፖሊስነት ዓለም አቀፍዊነት እሳቤ ያለው ሙያ መሆኑን ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ “የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ ቀን ከሌት በትጋት መስራት ይጠበቅበታል” ሲሉ ነው ያሳሰቡት።

የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሚፈልጉ ኃይሎችን እና የውስጥ ሰላማችንን ለመንሳት የሚፈልጉ ሕገ ወጦችን አደብ ለማስገዛት ብቁ የኾነ ኃይል እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ካከናወነው ሪፎርም ባሻገር ፖሊስ ተልዕኮውን ለማስፈጸም የሚያስችለውን አቅም ለማሳደግ ሰራዊቱን በአመራር ጥበቡም ሆነ በውጊያ ብቃቱ አቅሙን እንዲያጎለብት ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ ነው ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ያብራሩት።

ለሰላም መረጋገጥ የተደራጀ የሕዝብ ሃብት፣ ብቃት እና ቁርጠኝነት ያለው የጸጥታ ኃይል ይጠይቃል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የተሟላ ግንዛቤ እና የጠራ አመለካከት ያለው የፖሊስ ኃይል መገንባት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የፖሊስ ተቋም ከሌሎች የፍትህ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራሩን በማዳበር የአማራን ህዝብ የፍትህ ፍላጎት እና የፍትህ ጥያቄ ባፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይገባል ሲሉ ነው ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በእውቅና እና ሽልማት መርሐ-ግብሩ ላይ አጽንኦት ሰጥተው ያሳሰቡት።

በፕሮግራሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ የአማራ ክልል ፖሊስ የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት የመጠበቅ እንዲሁም ልማት እና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በማክበርና በማስከበር ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ ባሳለፍናቸው ተከታታይ አመታት በህግ ማስከበር ተግባር ቀን ከሌት በመስራት ህገወጥ ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ለመከላከል ሰራዊቱ ከህይወት መስዋዕትነት ባሻገር ቤተሰቡን ጭምር አደጋ ውስጥ በሚጥል ሁኔታ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል ብለዋል።

አሁን ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊት የአማራን ህዝብ ሰላም እና ደኅንነት የመጠበቅ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራሮች እና አባላትን እውቅናና ማበረታቻ መስጠት በተቋሙ አሰራር የተቀመጠ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ የዛሬው የማዕረግ አሰጣጥ ስነ-ስርዓትም ይህንን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም ለሁሉም የአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊት የማንቂያ ደወል መሆኑን ያስታወቁት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በቀጣይ አሰራራችንን በማዘመን ጀብድ ለሚፈጽሙ እና የላቀ አፈጻጸም ለሚያስመዘገቡ የሰራዊቱ አመራሮች እና አባላት እውቅናና ማበረታቻ በመስጠት የፖሊስን ከፍታ የምናስቀጥል ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።

እውቅናና ማበረታቻ የተሰጣችሁ አመራሮች እና አባላት ለተሻለ ስራ በመነሳሳት ህዝብ እና መንግስት የተጣለባችሁን ድርብ ኃላፊነት እንድትወጡ ብለዋል።

መላው የክልሉ የፖሊስ ሰራዊትም ከተበረታቱት ልምድ በመውሰድ እና በጎ የሆነ ተወዳዳሪነትን በማዳበር በቀጣይ ለምናካሂደው የእውቅናና የሽልማት ፕሮግራም እራሳችሁን እንድታዘጋጁ ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ አሳስበዋል።

በመርሐ-ግብሩ ለወንድ 3096 ለሴት 107 በድምሩ= ለ3203 የሰራዊቱ አባላት እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን ለአማራ ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲሉ ጀብድ ተፈጽመው ለተሰው የሰራዊቱ አመራሮች እና አባላት ቤተሰቦችም የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top