የ11ኛው የጣና ፎረም የባህር ዳር ከተማ ቆይታ በስኬት ተጠናቅቋል።
11ኛው የጣና ፎረም ከዛሬ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተሞች እየተካሄደ ነው።
የዛሬው የፎረሙ መክፈቻ በውቢቷ በባህር ዳር ከተማ ውስጥ ተካሂዷል። ቀጣይ የፎረሙ መርሐ ግብሮችም በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ ይኾናል።
በባህር ዳር ከተማ የነበረውን ቆይታ አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የ11ኛው የጣና ፎረም የባሕር ዳር ከተማ ቆይታ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።
የባህር ዳር ከተማ ልዩ ምልክት በሆነው ጣና ፎረም ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ከዋዜማው ጀምሮ በመቀበል በከተማዋ ውስጥ የሰመረ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማስቻል የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቂ ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር ተናግረዋል።
ይህም እንግዶች ከፎረሙ ጎን ለጎን ባህር ዳር ከተማን እና በጣና ሐይቅ ላይ የተሠሩ ልማቶችን ተዘዋውረው እንዲያዩ እና ያማረ ቆይታ እንዲኖራቸው አስችሏል ነው ያሉት።
እንግዳ ወዳዱ የባህር ዳር ሕዝብም እንግዶቹን ተቀብሎ እሴቱን በጠበቀ መልኩ አስተናግዷል፤ ምሥጋናም ይገባዋል ብለዋል።
የጣና ፎረም ስኬት ባህር ዳር ከተማ ያካበተቸውን ዓለም አቀፍ መድረኮችን የማዘጋጀት ብቃት ያስመሰከረ እንደሆነም ተናግረዋል።
በቀጣይም እንዲህ ዓይነት ዓለም አቀፍ፣ አሕጉራዊ እና ሀገር አቀፍ ጉባኤዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ማካሄድ ቢፈለግ አስተማማኝ የማስተናገድ አቅም አለ ነው ያሉት።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ የጸጥታና ደኅንነት ግብርኃ-ይሉ ማለትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ እንዲሁም የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ ከመቸውም ጊዜ በላይ የተናበበ እና ጠንካራ ስምሪት የታየበት እንዲሁም ቀን እና ሌት በቁርጠኝነት እና በትኩረት ስራዎች የተሰሩበት፤ ለቀጣይም ልምድ የሚወሰድበት ስምሪት ነበር ብለዋል።
ለጣና ፎረም ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን በሙሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አመስግነዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ እና አክባሪ ነው፤ ከአፍሪካ እና ከመላው ዓለም ወደ ክልሉ የመጡ እንግዶቹን ተንከባክቧል ነው ያሉት።
እንግዶች በባህር ዳር ከተማ ውስጥ በቀን እና በምሽት እየተዘዋወሩ የከተማዋን ውበት እና ልማት ተመልክተዋል ብለዋል።
ቆይታቸው ያማረ እና የፎረሙን ዓላማ ያሳኩበት እንደነበረም ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ 11ኛው የጣና ፎረም በሰላም መካሄዱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ያብራሩት።












