የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና የክልሉ ፍትሕ ቢሮ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በክልሉ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት እና በሕግ የበላይነት ማስከበር ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ በዛሬው ዕለት ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው በፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያው አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እና በፍትሕ ቢሮ ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ጎሹም ሲሆን፣ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ባደረጉት ንግግር፣ ሰነዱ የፖሊስን የሥራ አፈጻጸም ጥራት ከማሻሻል ባሻገር በሕግና በሥርዓት የተመሠረተ የጸጥታ አካባቢ ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ ይህ የመግባቢያ ሰነድ በዋነኛነት ዓላማው በወንጀል ምርመራ፣ ክስ ዝግጅት፣ የሕግ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዲሁም በሌሎች የፍትሕ ዘርፎች የሁለቱን ተቋማት ቅንጅትና ትብብር ማጠናከር ነው።
ሙያዊ ስነምግባርን እና መንግስታዊ ኃላፊነትን በማክበር እና ከወገንተኝነት የራቀ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመስራት የተሻለ የፍትህ ስርዓት እንዲረጋገጥ የጋራ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ አስፈልጓል ሲሉ ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ያብራሩት።
ከተቋም ግንባታና ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ባሻገር የህዝብን የፍትህ ችግር መፍታት ይገባል ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ይህን የስምምነት ሰነድም እስከ ታኛው መዋቅር ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን የፍትህ ስርዓት ማስተካከል ይገባል ብለዋል።
አቶ ብርሃኑ ጎሹም የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው፣ የመግባቢያ ሰነዱ በክልሉ ለሚከናወነው የሕግ የበላይነት ማስከበር ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ እና ተቋማዊ ትብብርን ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ብርሃኑ ጎሹም ገለጻ በህዝብ ዘንድ ታማኝነትንና ቅቡልነትን ያላበሰ የፍትህ ስርዓትን ለማረጋገጥ የክልሉ ፖሊስ እና ዐቃቢ ህግ በጋራ ሊሰራ ይገባል።
ለወንጀል መከላከልም ሆነ ወንጀል ምርመራ ስራ ውጤታማነት ስምምነቱ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ በቅብብሎሽ ሳይሆን በመተጋገዝ እና በመተባበር በመስራት የህዝብን የፍትህ ፍላጎት ለመመለስ ያስችላል ሲሉ ነው አቶ ብርሃኑ ጎሹም አክለው የተናገሩት።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አሰራሩ የፍትህ ስርዓትን ለማጎልበት ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተው፤ አተገባበሩ እስከ ዞን እና ወረዳ በማድረስ በቴክኖሎጅ የታገዘ አሰራርን ለማጎልበት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የፍትሕ አስተዳደሩን ሂደት ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በጋራ መሥራት የሚያስችሉ ዝርዝር የአፈጻጸም ነጥቦች በሰነዱ ውስጥ መካተታቸውም ታውቋል።
በመጨረሻም፣ ሁለቱ ተቋማት የመግባቢያ ሰነዱን በጽኑ በመተግበር በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ እንዲሁም የዜጎች የፍትሕ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
በስምምነት ሰነድ ፊርማው ላይ የተገኙት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቹ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
















