በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የጣና ፎረም ጉባኤ በሰላም እንዲካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተከናውኗል።

በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የጣና ፎረም ጉባኤ በሰላም እንዲካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተከናውኗል።

የአፍሪካ መሪዎች፣ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እና ምሁራን የሚሳተፉበትን ይህን ታላቅ ስብሰባ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዘጋጅነት የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ በዕቅዱ ላይ ውይይት አካሂደዋል።

በዕቅድ ውይይቱ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራተጂክ አመራሮች እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ተሳትፈዋል።

ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በዕቅድ ውይይቱ እንዳስታወቁት በዋና ዋና መንገዶች ላይ የትራፊክ ፍሰትን የሚያቀላጥፉ እና የጸጥታ ስራን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ በተለይ እንግዶች በሚያርፉባቸው ሆቴሎች እና ስብሰባው በሚካሄድበት አዳራሽ ዙሪያ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ይከናወናሉ።

የቅድመ ዝግጅት ስራው የከተማዋን አንጸባራቂ ገፅታ ከመጠበቅ ባለፈ፣ ስብሰባው ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በሰላምና በታቀደው ልክ እንዲጠናቀቅ የሚያደርግ አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በዕቅድ ውይይቱ ላይ አጽንኦት ሰጥተው ያብራሩት።

እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የጣና ፎረም የሀገር መሪዎች እና ዲፕሎማቶች የሚታደሙበትና አህጉራዊ የጸጥታ ሁኔታዎች ተገምግመው አህጉራዊ መፍትሔ የሚቀመጥበት ሁነት ነው ብለዋል።

እንደ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) ገለጻ በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የጣና ፎረም ዓለም አቀፍ ስብሰባ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ገፅታ በመገንባት ረገድ ሚናው የላቀ ነው።

ሁነቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ኃይሉ ማህበረሰቡን ከጎኑ በማድረግ የተጣለባችሁን ህዝባዊ ኃላፊነት በአግባቡ ልትወጡ ይገባል ሲሉ ነው እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) ያሳሰቡት።

ከዕቅድ ውይይቱ መጠናቀቅ በኃላ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው 11ኛው የጣና ፎረም ዓለም አቀፍ ስብሰባ በሰላም እንዲካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ በመግለጫው አንስተዋል።

በርካታ የአፍሪካ መሪዎች፣ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እና ምሁራን የሚሳተፉበትን ይህን ታላቅ ስብሰባ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድ የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በዕቅዱ ላይ ውይይት ማካሄዱንም ገልጸዋል።

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በክልሉ የሚከናወኑ ታላላቅ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የሚያስችል አቅም እና ልምድ ያለው መሆኑን ረዳት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የጸጥታ ኃይሉ ከከተማው ማህበረሰብ እና ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ጥበቃው ለ24 ሰዓት ይከናወናል ነው ያሉት።

እንግዶች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የትራፊክ ፍሰቱ በተሳለጠ መልኩ እንዲከናወን ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ሲሉ ነው ያከሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ።

የከተማው ማህበረሰብ፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው ሰላም እና ደኅንነትን ለማስከበር በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

እንግዶች በሚንቀሳቀሱበት ማንኛውም ቦታ ህብረተሰቡ ቅድሚያ በመስጠት እና በማክበር የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነውን እንግዳ ተቀባይነትን በተግባር ልናረጋግጥላቸው ይገባል ብለዋል።

እንደ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ገለጻ ያለህብረተሰቡ ተሳትፎ ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ አይቻልም፤ ስለሆነም የከተማው ህብረተሰብ እና ወጣቱ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ሰላም እና ጸጥታ እንዲከበር እየተሰራ ይገኛል።

ህብረተሰቡ በአካባቢው የተለየ እንቅስቃሴ እና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለጸጥታ ኃይሉ ፈጥኖ ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስባለሁ ሲሉ ነው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ያብራሩት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top