ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ጥይት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ አስታውቋል።
ኮማንደር ደሳለኝ አበራ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ እንደገለጹት መነሻውን ከገንዳውኃ ከተማ ጥጥ መዳመጫ በማድረግ መዳረሻውን ጎንደር ከተማ ያደረገ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ -3 አ.አ 18701 አይ ሱ ዙ የጭነት ተሽከርካሪ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ጥይት ከጭነት ጋር በመደበቅ ሲያዘዋውር በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በላይ አርማጭሆ ወረዳ በትክል ድንጋይ ከተማ ልዩ ቦታው አይነት ውኃ ከተባለው አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
ከጫነው የጥጥ ጭነት ውስጥ በመደበቅ እያዘዋወረ የነበረውን 2218 የብሬን እና 1311 የM-14 ጥይት እንዲሁም ስድስት የብሬን ሸንሸል እና ስድስት ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከህብረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ እና በጸጥታ ኃይሉ ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ኮማንደር ደሳለኝ አበራ አስረድተዋል።
በተጨማሪም መነሻውን ከገንዳውኃ ከተማ ያደረገ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በላይ አርማጭሆ ወረዳ በትክል ድንጋይ ከተማ ልዩ ቦታው አይነት ውኃ ከተባለው አካባቢ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 1386 የብሬን ጥይት በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮማንደር ደሳለኝ አበራ አክለው ገልጸዋል።
ከህገ-ወጥ ድርጊቱ ጋር በተያያዘ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል ሲሉ ኮማንደር ደሳለኝ አስረድተዋል።
በቁጥጥር ስር የዋለው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ጥይት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ህገ-ወጥ ቡድን ቢደርስ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ እንደነበር የፖሊስ አዛዡ አብራርተዋል።
ህዝቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ለሚደረገው ድጋፍ ምስጋና ይገባዋል ያሉት ኮማንደር ደሳለኝ በቀጣይ መሰል ህገ-ወጥ ድርጊት ሲመለከት ለጸጥታ ኃይሉ ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።






