የ34ኛ ዙር የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ምልምል ፖሊሶች የስልጠና ሂደት ጉብኝት ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እና የክልሉን የጸጥታ ስጋት ለመቆጣጠር ልዩ ልዩ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል።
ከተግባራቱ መካከል ምልምል ፖሊሶችን በማሰልጠን የፖሊስን አገልግሎት ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የ34ኛ ዙር መደበኛ እና የአድማ መከላከል ሰልጣኝ ምልምል ፖሊሶችን በብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እያሰለጠነ ይገኛል።
ረዳት ኮሚሸነር ታደሰ አያሌው ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ እና ሌሎች ስትራቴጅክ እና ከፍተኛ አመራሮች የስልጠና ሂደቱን ጎብኝተዋል።
ፖሊስ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት በመራቅ የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ ነው ሲሉ ረዳት ኮሚሸነር ታደሰ አያሌው ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ገልጸዋል።
ወንጀልን ቅድሚያ በመከላከል ላይ ያተኮረ አሰራርን በመከተል ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ምርመራ በማጣራት አጥፊው በህግ እንዲጠየቅ በማድረግ ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ ከፖሊስ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አክለው ተናግረዋል።
ክልሉ ችግር በገጠመው ጊዜ ግንባር ቀደም በመሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ፖሊስ ተቋምን መቀላቀላችሁ የሚያስመሰግናችሁ ተግባር ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ስልጠናችሁን አጠናቃችሁ ስትመደቡ የክልላችንን ህግ የማስከበር አቅም ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ፖሊስነት በርካታ ውጣ ውረዶችን የሚያሳልፍ፣ ቁርጠኛ፣ ትግዕሰተኛ፣ በቅንነት ህዝብን የሚያገለግል እንዲሁም ሰብዓዊነትን የሚያስቀድም ሙያ ነው ብለዋል።
ፖሊስነት ለሰላም መከበር እስከ ህይወት መስዕዋትነት መክፈልን የሚጠይቅ ሙያ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የሚሰጡ የመስክ እና የክፍል ትምህርቶች ይህን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
ለነገ የህዝብ እና የመንግስት የተቋም ተልዕኮዎች ራሳችሁን ዝግጁ በማድረግ ቀሪ የስልጠና ጊዜያችሁን በውጤታማነት እንድታጠናቅቁ በማለት ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ አሳስበዋል።
ኮማንደር አብዮት ሽፈራው የዋና ጠቅላይ መምሪያው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሰልጣኝ ምልምል ፖሊሶች ከሁሉም የክልላችን አካባቢዎች ተመልምለው የመጡ መሆኑን ጠቅሰው ውስብስብ የምልመላ ሂደቶችን አልፋችሁ ማህበረሰቡን ለማገልገል የፖሊስ ሙያን መርጣችሁ እና ፈቅዳችሁ ተቋሙን መቀላቀላችሁ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በሪፎርም ላይ መሆኑን የገለጹት ኮማንደር አብዮት የዛሬ ሰልጣኞች የነገ ተመራቂ ምልምል ፖሊሶች ይህንን ተገንዝባችሁ ለጋራ ውጤት ዝግጁ እንድትሆኑ በማለት አሳስበዋል።
በመጨረሻም አስተያየት የሰጡት ምልምል ሰልጣኝ ፖሊሶች እንደዚህ አይነት ስልጠና ይሰጣል ብለው እንዳልገመቱ እና አሁን ላይ ሙያዊ ብቃትን የሚያሳድግ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ወደፊት የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ግዳጅ ተቀብለው በብቃት እንደሚፈጽሙም አረጋግጠዋል።







