“መለዮ ለባሽና ሠንደቅ ዓላማ የጠበቀ ሚስጢር፣ የረቀቀ ፍቅር እና ጥብቅ ግንኙነት አላቸው።” አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 18ኛውን ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በባህርዳር ከተማ ባከበረበት ቀን ተገኝተው ንግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ሠንደቅ ዓላማ እና መለዮ ለባሽ ኃይል ከጥንት የጀመረ ጥብቅ ቁርኝትና ፍቅር ያላቸው የሀገራችን የሉዐላዊነት መገለጫ ናቸው ብለዋል።
የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን ከወትሮው የተለየ የሚያደርገው ሀገራችን በስኬት ያጠናቀቀቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ስራ በጀመሩበት እና የከፍታ ዘመን መጀመሪያ ላይ መሆኑ ነው ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ጀግኖች ለሀገራችን ሉዓላዊነት መጠበቅ የከፈሉትን ዋጋና ክብር ለማስታወስ የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ትልቅ ዋጋ አለው ሲሉ አክለዋል።
እንደ አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጻ የባዳና ባንዳ አጀንዳን በማከክሸፍ ለሀገራችን ክብር እና ሰላም ዋጋ እየከፈሉ ላሉ የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ አካላትም ክብር ይገባችኋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ በበኩላቸው የሀገራችን ሠንደቅ ዓላማ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች የሚወክል በመሆኑ እና ሁሉም ዜጋ ለሀገር ፍቅር እና ክብር የከፈለውን ዋጋ የሚያስታውስ ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚገጥማትን ሳንካ በጀግና ልጇቿ እየፈታች እና በመስዋዕትነት እያረጋገጠች ያለች ሀገር ናት ሲሉ ምክትል አፈ-ጉባኤው አብራርተዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ቀን በዓለም አደባባይ በሠንደቋ የደመቀች ሀገር መሆኗን ያስመሰከረች ሉዓላዊነት ሀገር መሆኗን ለማብሰር የሚከበር በዓል ነው ሲሉም አቶ አማረ ሰጤ አክለው ተናግረዋል።
ባህር ዳር ከተማ የተከበረው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ሁነቶች የታጀበ ነው።
በበዓሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊት፣ የፖሊስ ማርች ባንድ እና የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት የተለያዩ የሰልፍ ትርዒቶችን አሳይተዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት በገባ የመጀመሪያው ሰኞ ላይ የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም ለ18ኛ ጊዜ ‘ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጲያ ሕዳሴ’ በሚል መሪ ቃል በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ተከብሯል።

















