በኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም እየተከበረ ነው።

በኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም እየተከበረ ነው።

ቀኑ ‘ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጲያ ሕዳሴ’ በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው።

በዓሉን አስመልክቶ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ሠንደቅ ዓላማ ሲነሳ ከሚታወሱት መካከል አንዱ ፖሊስ መሆኑን ገልጸዋል።

ፖሊስ መሰረታዊ የፖሊስ ስልጠናውን አጠናቅቆ ሲመረቅ ቃለ መሀላ የሚፈጽመው በሠንደቅ ዓላማ ፊት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሠንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የነጻነት፣ የጀግንነት እና የአንድነት መገለጫ ነው። ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው ፖሊስ ስራውን ሲጀምር ስለሠንደቅ ዓላማ እያሰበ የሚሆነው ብለዋል።

ሠንደቅ ዓላማችን የሰላም እና የነጻነት ምልክት ነው፤ ለፖሊስም ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ፖሊስ ለህዝብ ክብር እና ለሀገር ሉዓላዊነት በግንባር ቀደምነት ሲሰለፍ ሠንደቅ ዓላማን አንግቦ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሠንደቅ ዓላማ ለፖሊስ ከፍ ያለ ስሜት፣ ትርጉም እና ክብር ያለው ነው። ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል የህዝብ ሰላምን ከመጠበቅ እና ወንጀለኛን ለሕግ በማቅረብ ፍትህን ከማስፈን ጎን ለጎን ህብረተሰብን በሚያገለግልባቸው የስፖርት እና የኪነ ጥበብ ዘርፍም ለሠንደቅ ዓላማ ክብር እና ከፍታ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያም የሠንደቅ ዓላማ ማውጣት እና ማውረድ ስነ ስርዓትን የሪፎርሙ አካል አድርጎ እየሰራ ነው። በመኾኑም በዓመት አንድ ቀን በዓል ማክበር ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ለሠንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር እየተከወነ ነው። በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ እና በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስ አባላት ትምህርት የሚወስዱበት ነው ብለዋል። በዞን እና ወረዳዎችም የሠንደቅ ዓላማ ክብር እንዲጠናከር እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ስለ ሰላም በመወያየት፣ ሁሉም የሰላም ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው በማለት ስለ ሰላም በመነጋገር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top