“ባዳ እና ባንዳዎች በፈጠሩት አሻጥር የተፈጠረውን ግጭት ለመከላከል የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ተግተው በመስራት እስከ ህይወት መስዕዋትነት ድረስ ከፍለዋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ተመስገን ጥሩነህ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሪፎርም ሥራ፣ የዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንፃ የምረቃ መርሀ-ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢፌዲሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጀኔራል መኮንኖች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ተመስገን ጥሩነህ “ባዳ እና ባንዳዎች በፈጠሩት አሻጥር የተፈጠረውን ግጭት ለመከላከል የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ተግተው በመስራት እስከ ህይወት መስዕዋትነት ድረስ ከፍለዋል” ብለዋል።
የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ የምስረታ ታሪክ ትልቅ ሚና ያለው ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ተመስገን ጥሩነህ የክልሉን ህዝብ ሰላም የሚነሱ አካላት የተከበረውን የአማራ ህዝብ የማይወክሉና የውጭ ጠላት ሴራ ፈፃሚ ናቸው ነው ያሉት።
የክልሉ ፖሊስ የሪፎርም ስራዎች ተቋሙን ወደ ከፍታ የሚያሻግሩ ናቸው፤ ይህም ተቋሙ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ የትላንቱ መነሻ፣ የነገው ደግሞ መዳረሻሻ ነውና ውጤታማ ተግባር እንዲሆን ጠንክሮ መስራት ይጠይቃል ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አብራርተዋል።
ፖሊስ ከፅንፈኛ አስተሳሰብ፣ ከጎጠኝነት እና ከሌብነት ፍፁም የጸዳ መሆን አለበት በማለት ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
የአማራ ክልል ፖሊስ የክልሉን ህዝቡ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ህገ መንግስቱን ለማስከበር የገባውን ቃል አክብሮ ለመስዕዋትነት የማያመነታ ሰራዊት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ለፖሊስ ተቋሙ የሪፎርም ስራዎች የክልሉ መንግስት በእኔነት ስሜት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ያካሄደው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራ የክልሉን ሰላም ይመልሳሉ ተብለው የታመኑ ጉዳዮችን ለማስተካከል የተደረገ እንደሆነም አብራርተዋል።
ሪፎርሙ በሁሉም የፖሊስ የስራ ዘርፎች ውስጥ ቴክኖሎጂን ተጠቃሚ ያደረገና ከዘመኑ ጋር ተራማጅ የሆኑ አሰራሮችን ያካተተ በመሆኑ ለዚህ የሪፎርም ስራ መሳካት ዋጋ የከፈላችሁ የፖሊስ ተቋሙ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም አጋር አካላት ክብር ይገባችኋል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናግረዋል።
አሁን ያለው የፖሊስ አደረጃጀት በፊት ከነበረው የተሻለ በመሆኑ የሰራዊቱ ሞራልም በከፍተኛ ደረጃ መነሳሳትን የፈጠረ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን ህዝብ የሰላም ጥያቄ መመለስ የዚህ ተቋም ርዕይ እና ግብ መሆኑንም ገልጸዋል።
የተጠናከረ፣ የዳበረ እና በህዝብ ዘንድ ታዓማኒነትን ያተረፈ የጸጥታ ኃይል ለመገንባት ከተጀመረው የፖሊስ የሪፎርም ስራዎች በተጨማሪም በሌሎች የክልሉ የጸጥታ ተቋማትም ሁለንተናዊ የሪፎርም ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ የተደራጁ ወንጀለኞችንና ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በራሳችን አቅም ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የአድማ መከላከል፣ የፈጥኖ ደራሽ፣ የመሰረተ ልማት ጥበቃ፣ የኢንዱስትሪና የጀልባ ላይ ጥበቃ ፖሊስን በማዋቀር ፖሊስ የወንጀል መከላከል ተግባሩን በብቃት እና በፍትሃዊነት እንዲከውን መደላድል የተፈጠረበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ስራችን የፖሊስና የህዝብ አጋርነትን በማጎልበት ችግሮችን በጋራ ለይቶ መፍትሔ ለመስጠት እና ፖሊስ የህዝብ ቅቡልነትን እንዲያገኝ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች እንደተጠናከረ አብራርተዋል።
የሰራዊቱን አቅም ለማጎልበት በሙያዊ ስነ-ምግባር፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝና በዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ቴክኒኮች ላይ በቂ ስልጠና እንዲያገኝ ተቋሙ ፍኖተ-ካርታ እና የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር ስትራቴጅ ተቀርጾ ተግባራዊ ተደርጓል ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በህግ ማስከበር ስራው ውጤታማ የሆኑትን ከስትራቴጅክ አመራር እስከ አባላት ድረስ ወንድ= 3,171 ሴት= 96 በድምሩ= 3,267 አመራር እና አባላት በልዩ ልዩ የማበረታቻ አይነቶች እንዲበረታቱ የተደረገ ሲሆን፤ የተደረገው ማበረታቻ የፖሊስ ሰራዊቱ ለሚያደርገው የህግ ማስከበር ስራና ለክልላችን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ የበለጠ እንዲተጋ ያደርገዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሪፎርም ስራ፣ የዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንፃ የምረቃ መርሀ-ግብር ላይ ለተቋሙ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ዕውቅናና የሽልማት ተበርክቶላቸዋል።












