“የፖሊስ ተቋምን በማዘመን ወደ ከፍታ ማማ በመውጣት የአማራ ክልልን ህዝብ ሰላም እና ደኅንነት እናረጋግጣለን!!”
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የዋና ጠቅላይ መምሪያው የሪፎርም ስራ፣ የዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንፃ የምረቃ መርሀ-ግብር ላይ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት፦
የተከበራችሁ የክልላችን ነዋሪዎች፣ የፖሊስ ሰራዊት እና ባለድርሻ አካላት፣ የፖሊስ ተቋማችን አሁን ያለበትን ሁኔታ፣ እያከናወናቸው ያሉትን ወሳኝ የሪፎርም፣ የሰላም ማስፈን እና የህዝብ ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ቁርጠኝነትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎችን ለማከናወን ችለናል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በክልሉ ውስጥ ሰላምና ደህንነትን በመጠበቅና በክልሉ ህገ-መንገስታዊ ስርዓት እንዲከበር ቀን ከሌት ሰርቷል እየሰራም ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት አመታት የክልላችን ሰላም በጽንፈኛ ቡድኖች ሕገ-ወጥ ድርጊት በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል፤ በክልሉ የልማት ፕሮጀክቶችም ችግር ውስጥ ገብተዋል። ሆኖም የክልሉ መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አመራር፣ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል እና የክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ተቀናጅተው በወሰዱት ህግ የማስከበር ተግባር አንጻራዊ ሰላም የሰፈነ ሲሆን ቀጣይም ቀሪ ስራዎችን ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
ባለፉት አመታት በተለያዩ ጊዚያት የክልሉ ፖሊስ ተቋማዊ ሪፎርም ያካሄደ ቢሆንም ሪፎርሙ የተቋሙን መሰረታዊ ፍላጎት ያላሟላ፣ በየደረጃው ያለውን አመራርና አባላት በበቂ ከማሳትፍ አንጻር ውስንነቶች የነበሩበትና ክልሉ የገጠመው የጸጥታ ችግር ተደምሮ በቁልፍ የተቋሙ ችግሮች ዙሪያ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል።
እነዚህን ችግሮች የተረዳው የክልሉ መንግስት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እንዲሰራ ኮሚቴዎችን በማዋቀርና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በመፍቀድ እንዲሁም ሂደቱን በመከታተል ለሪፎርሙ ውጤታማነት ላቅ ያለ ድርሻ አበርክቷል።
ሪፎርማችን የፖሊስ የሙያ፣ የአሰራር፣ የተጠሪነት ጉዳይና ሌሎች በሪፎርሙ የተመለሱ የፖሊስ ሙያ በስታንዳደርድ እንዲሆን የክልሉ መንግሰትና የአስተዳደር ምክር ቤት ላሳለፈው ውሳኔ ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡
ተቋሙ የአሰራር ነጻነት እንዲኖረው እና የፖሊስን ዶክትሪን የተከተለ እንዲሆን የተጠሪነቱ ጉዳይ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያው ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተጠሪ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የክልሉ መንግስት ባጸደቀው መዋቅራዊ አደረጃት መሰረት ከክልል ጀምሮ በተዋራድ ባሉ የአመራርና የሙያተኛ የስራ መደቦች ስራ እና ሰራተኛን ለማገናኘት በሚያስችል መልኩ የአመራር ብቃትን፣ ስነ-ምግባርንና የትምህርት ዝግጅትን ለክልሉ ህዝብና መንግሰት ለማገለግል ያለውን ቁርጠኝነት ጭምር መሰረት ያደረገ ምደባ ተጠናቆ ወደ ስራ ገብተናል።
የተደራጁ ወንጀለኞችንና ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በራሳችን አቅም ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የአድማ መከላከል፣ የፈጥኖ ደራሽ፣ የመሰረተ ልማት ጥበቃ፣ የኢንዱስትሪና የጀልባ ላይ ጥበቃ ፖሊስን በማዋቀር ፖሊስ የወንጀል መከላከል ተግባሩን በብቃት እና በፍትሃዊነት እንዲከውን መደላድል ፈጥሯል።
በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ስራችንም የፖሊስና የህዝብ አጋርነትን በማጎልበት ችግሮችን በጋራ ለይቶ መፍትሔ በመስጠት እንዲሁም ፖሊስ የህዝብ ቅቡልነትን እንዲያገኝ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ተጠናክረዋል።
የሰራዊቱን አቅም ለማጎልበት በሙያዊ ስነ-ምግባር፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝና በዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ቴክኒኮች ላይ በቂ ስልጠና እንዲያገኝ ተቋሙ ፍኖተ-ካርታ እና የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር ስትራቴጅ ተቀርጾ ተግባራዊ ተደርጓል።
ተቋማዊ ሪፎርሙ ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖር ለማድረግ የክልሉ መንግስት ባደረገው ልዩ ድጋፍ ባለ ሰባት ወለል ህንጻ ተረክበናል። በተጨማሪም የዞን ፖሊስ መምሪያ እና የወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ቢሮዎች ለስራ ምቹ እንዲሆኑ የህንጻ ዲዛይን ተዘጋጅቶ በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ አይነት የቢሮ ግንባታ ለማስጀመር የዞንና የከተማ አስተዳደሮችን ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡
በህግ ማስከበር ስራ ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን የሰራዊቱ አባላት የጉዳት ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ ሆኗል። በክልል ደረጃ የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ለመጀመሪያ ጊዜ በአይነቱ ልዩ የሆነ በደብረብርሃን ከተማ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታ ተጀምሯል። በተጨማሪም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅን ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት እንዲሸጋገር በአስተዳደር ምክር ቤት ተወስኗል።
በህግ ማስከበር ስራው ውጤታማ የሆኑትን ከእስትራቴጅክ አመራር እስከ አባላት ድረስ ወንድ= 3,171 ሴት= 96 በድምሩ= 3,267 አመራር እና አባላት በልዩ ልዩ የማበረታቻ አይነቶች እንዲበረታቱ የተደረገ ሲሆን የተደረገው ማበረታቻ የፖሊስ ሰራዊቱ ለሚየደርገው የህግ ማስከበር ስራና ለክልላችን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ የበለጠ እንዲተጋ ያደርገዋል።
የተከበራችሁ የክልላችን ነዋሪዎች ማንኛውም ዜጋ በሰላም የመኖርና በነፃነት የመዘዋወር መብቱ እንዲከበር የሚያስችል በቴክኖሌጅ የተደገፈ አሰራርና አደረጃጀት አጠናቀን ወደ ተግባር የገባን ሲሆን በስራችን ስኬት ለማስመዝገብ የህዝብ ቅቡልነት፣ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ለፖሊስ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደምታደርጉ ተስፋ አደረጋለሁ፡፡
የፖሊስ ሰራዊቱም ለህዝብ ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ሙያዊ ስነ-ምግባርን በመላበስ እስከ ህይወት መስዕዋትነት ጭምር በመክፈል ለህዝብ የገባነውን ቃል በተግባር ለማረጋገጥ በቁርጠኝነትና በህዝብ አገልጋይነት ስሜት ስራችሁን እንደሚወጡ ለማረጋገጥ እወዳለሁ። በተጨማሪም ለህዝቡ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት አራት የማይታለፉ ቀይ መስመሮችን ማለትም ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በሐይማኖት ጣልቃ የማይገባ፣ ከሌብነት የራቀ እና ጎጠኝነትን የሚጸየፍ ሊሆን ይገባዋል።
አጋር አካላትም ለፖሊስ ተቋም ላደረጋችሁት ድጋፍ አክብሮቴን እየገለጽኩ፤ የሪፎርም ስራ በባህሪው በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን ሂደትን የሚፈልግ መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም ሪፎርማችን እንደ ማለዳ ፀሀይ ታይቶ የሚጠፋ እንዳይሆን እና ቀጣይ ለሚኖረን የከፍታ ጉዞ ሁሉን አቀፍ ትብብርና ድጋፋችሁ እንዳይለየን ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም ለሪፎርማችን ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ ለነበራችሁ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ለክቡር ጀኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ ለፌዴራል ፖሊስ ማኔጅመንት እና አመራር፣ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ለዞን እና ለከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ ለክልላችን የፖሊስ ሰራዊት፣ ለባለሀብቶች እንዲሁም ለፖሊስ ስራ አይተኬ ሚና ላላችሁ ለመላው የአማራ ክልል ህዝብ በእኔና በአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊት ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።
“የፖሊስ ተቋምን በማዘመን ወደ ከፍታ ማማ በማውጣት የአማራ ክልልን ህዝብ ሰላም እና ደኅንነት እናረጋግጣለን!!”
“በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል’’













