የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት አድርጓል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት አድርጓል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

እንደ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ገለጻ በክልሉ የሚከበሩ ህዝባዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የሚታደሙበት ስለመሆኑ አንስተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ከፌዴራል እና ከክልል የጸጥታ ኃይል ጋር በጥምረት የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሰላም እንዲከበር የተሟላ ዝግጅት አድርጓል ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጋር እንዲሁም ከሐይማኖት አባቶች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በዓሉን በሰላም ለማጠናቀቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የጸጥታ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ኦረንቴሽን ተሰጥቶ እና ውይይት ተካሂዶ ወደ ስራ መገባቱንም ጠቁመዋል።

ስኬታማ የሰላምና ደህንነት ስራን ለመስራትም የጸጥታ ኃይሉ ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ዜጎችን በሚገባ በማስተናገድና አጠራጣሪ ሁኔታ ሲስተዋል ጥቆማ በመስጠት ህዝቡ እንዲተባበርም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል የዳበረ አቅም አለው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ለበዓሉ ፍጹም ሰላማዊነት ሁሉንም የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅሞች እንጠቀማለን ብለዋል፡፡

የፖሊስ ኃይሉ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር የተንቀሳቃሽ እና ቋሚ ጥበቃ ተመድቦ ተግባሩን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በሚካሄድባቸው ስፍራዎች ሊከሰት የሚችልን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ የጸጥታ ኃይሎች ለሚያስተላልፉት መልዕክት የበዓሉ ታዳሚዎች እና አሽከርካሪዎች ቀና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ህብረተሰቡ ከፖሊስ የሚተላለፉ ክልከላዎችን በማክበር የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ አሳስበዋል።

የመስቀል ደመራ በሚደመርበት ወቅት ርችት ወይም ማንኛውንም ተተኳሽ መተኮስ የተከለከለ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ጸረ ሰላም ኃይሎች በርችት ሰበብ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጥሩ ህብረተሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ሲሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top