“ከራስ አልፎ ወገንን የሚጠቅም ስራ መስራት ለነገ የማይተው ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ለነጋችን ዛሬ ላይ መሰረት መጣል ግዴታችን ነው” ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ

“ከራስ አልፎ ወገንን የሚጠቅም ስራ መስራት ለነገ የማይተው ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ለነጋችን ዛሬ ላይ መሰረት መጣል ግዴታችን ነው” ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ በ2018 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።

ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ በሚከናወኑ ጉልህ ተግባራት ዙሪያ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ ዕቅዱን አጽድቋል።

ዕቅዱን ያቀረቡት የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አብዮት ሽፈራው በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች ያሉ የፖሊስ አመራርና አባላትን አቅም ሊያሳድጉ የሚችሉ ስልጠናዎችን መስጠትን ጨምሮ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል የፖሊስ ሰራዊት መገንባት ከተያዙ ዕቅዶች መካከል መሆኑን አብራርተዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ የተወደደና የተከበር ሰራዊት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት

ኮማንደር አብዮት የህዝቡን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ የወንጀል መከላከል አቅምን ማሳደግ ይገባል ሲሉ አክለዋል።

የጀልባ ተቆጣጣሪ ፖሊስ ስልጠና መስጠት፣ አዲስ የፖሊስ ጋራጅ ግንባታ፣ በትግል ለተጎዱ የሰራዊት አባላት የሚያገለግል የጀግኖች ማዕከል እና መሰል ተቋሙን ወደ ከፍታ ሊያሻግር የሚችሉ ተግባራት በትኩረት ሊሰሩ ከታቀዱት መካከል መሆናቸውን ነው ኮማንደር አብዮት የገለፁት።

በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ የያዝነው በጀት ዓመት የተቋሙ የመጭዎቹ አስር ዓመታት የዕቅድ ፍኖተ ካርታ እርሾ የሚጣልበት ዓመት እና ለግባችን መዳረሻ የመስፈንጠሪያ ዓመት በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም ፖሊስ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ከተያዙ የበጀት ዓመቱ ዕቅዶች መካከል እስከ ወረዳ ድረስ ያላለቁ የኃላፊዎች እና የባለሙያ ምደባን በፍጥነት በማጠናቀቅ ተቋምንና ህዝብን የሚጠቅም የሪፎርም ስራን እውን ማድረግ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ለዕቅዱ መሳካት የሁላችንም ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ከራስ አልፎ ወገንን የሚጠቅም ስራን መስራት ለነገ የማይተው ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ለነጋችን ዛሬ ላይ መሰረት መጣል ግዴታችን ነው ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

የተቀመጠው ዕቅድ አካታች፣ ለስራ ተነሳሽነትን የሚያጎለብት፣ የተቋሙን የከፍታ ዘመን አመላካች እንዲሁም የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት በቁርጠኝነት ለማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ያብራሩት የዕቅድ ውይይቱ ተሳታፊዎች ለዚህም ራስን ከወዲሁ ማዘጋጀት ይኖርብናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top