የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያካሄደ ባለው የሪፎርም አተገባበር እና አፈፃፀም ዙሪያ ውይይት አካሄደ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያካሄደ ባለው የሪፎርም አተገባበር እና አፈፃፀም ዙሪያ ውይይት አካሄደ

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያከናወነ ባለው የሪፎርም አተገባበርና አፈፃፀም ዙሪያ የጠቅላይ መምሪያ አዛዥች፣ የዋና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የመምሪያ እና የዋና ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት ነው ውይይቱ የተካሄደው።

ከሪፎርም ትግበራ ጀምሮ እስከ አሁን የተከናወኑ ስራዎችን እና አፈፃፀማቸውን አስመልክቶ ሰነድ ያቀረቡት ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ የፖሊስ ተቋም ከሌሎች የሚለየው በተለያዩ መስዕዋትነቶች ተቃኝቶ የተገነባ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ሪፎርሙ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተቋም ግንባታ እና ማስፋፊያ ዙሪያ፣ በቢሮ ዕድሳት፣ በሰው ኃይል አደረጃጀትና የኃላፊዎች ምደባ በኩል በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን የተሻለ አፈፃፀም የታየበት እንደሆነም ገልፀዋል።

ሪፎርሙ ጠንካራ የፖሊስ ሰራዊት የመፍጠር፣ ሰራዊቱን የመለወጥ እና ለስራ የመነሳሳት ተስፋዎች የታዩበት መሆኑን አብራርተዋል።

ህዝብን በቅንነት የሚያገለግሉ አመራሮች ወደ ፊት የመጡበት እንዲሁም የፖሊስን የከፍታ ዘመን የሚያመላክቱ በርካታ ስራዎች የተከወኑበት መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ በሰነዱ አመላክተዋል።

ሪፎርሙ ከክልል ዋና መምሪያ ኃላፊዎች እስከ ወረዳ ክፍል ኃላፊዎች ምደባ የተደረገ ሲሆን በቀጣይም የባለሙያ ምደባ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

አዲስ የቢሮ ግንባታን ጨምሮ ቢሮዎችን ለስራ ምቹ ማድረግ፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የአዳራሽ እድሳት እና ሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች የተገነቡበት መሆኑም ምክትል ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሰነድ ተጠቅሷል።

በሰው ኃይል ምደባና አያያዝ ብቃትንና ችሎታን መሰረት ያደረገ ምደባ የተደረገ ነው ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

የህንጻ ግንባታን እና የባለሙያ ምደባን በፍጥነት በማጠናቀቅ የምንሰጠውን አገልግሎት ጥራት ያለው እና ተደራሽ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ።

ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሪፎርሙ በርካታ አንፀባራቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት በመሆኑ እራሳችንን በዚህ ልክ በማብቃት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ይህን ለማድረግም ተቋምን ከራስ ፍላጎትና መሻት አስበልጦ በማየት በመተባበር፣ በመተጋገዝ እና በትጋት በመስራት የህዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ አለብን ሲሉ ነው ያብራሩት።

ሪፎርሙ የአሰራር ውስብስብነትን ያስቀረ፣ ቀላልና ፈጣን አሰራርን ያመጣ፣ የስራ ተነሳሽነትን የፈጠረ፣ የፖሊስን የቀደመ ክብር ያጎናፀፈ በመሆኑ ራስን በሪፎርሙ ልክ አብቅቶና አዘጋጅቶ የህዝብን የሰላምና የፍትህ ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለስ ይጠበቅብናል ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊ አመራሮች አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top