የአማራ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ አስቀመጠ።
የአማራ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት ዛሬ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ ገምግሟል። በግምገማው የክልሉ የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተገልጿል።
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ምክር ቤቱ የክልሉን አጠቃላይ የጸጥታ ሁኔታ መገምገሙን ተናግረዋል።
የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ከባለፉት ጊዜያት በእጅጉ እየተሻሻለ፣ ህዝቡም የሰላሙ ባለቤትና ተጠቃሚ እየኾነ መምጣቱን ምክር ቤቱ ገምግሟል ብለዋል።
በጫካ የነበሩ ታጣቂዎችም የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ እና ስልጠና እየወሰዱ ወደ ማኅበረሰቡ እየተቀላቀሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች ህዝባችን ሰላም ማግኘት አለበት፣ እስካሁን የበደልነውን ሀህዝብ መካስ አለብን ብለው እየተመለሱ መሆናቸውን አንስተዋል። እስካሁን ያጠፉትን ጥፋት ለመካስ ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል።
የጸጥታ ምክር ቤቱ የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ ያለውን ስራ መገምገሙንም ተናግረዋል።
ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክር ቤቱ አመላክቷል ነው ያሉት።
በክልሉ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለማሸጋገር በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።
የጸጥታ ምክር ቤቱ የትምህርት እና የልማት ሥራዎችንም መገምገሙን አንስተዋል። የትምህርት እና የልማት ስራዎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ መነሳቱን አብራርተዋል።
የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በቀጣይነት እየገመገመ ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲመለስ እንደሚሰራም አንስተዋል።
ምክር ቤቱ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም ለማምጣት ሁሉን አቀፍ ስራ እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት አባላት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል።









