የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ መግለጫ ሰጥተዋል።
በክልሉ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በጸጥታ ኃይሉና በህዝቡ ትብብር አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ወደ ነበረበት ሰላም እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የተገኘውን ሰላም በማጽናት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑንም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ በሰጡት በመግለጫ አንስተዋል።
የ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን መላው የክልሉ ህዝብ በሰላም እንዲያከብር የጸጥታ ስራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ከክልል እስከ ታችኛው የጸጥታ መዋቅር ድረስ ውይይት ተካሂዶ እና ኦረንቴሽን ተሰጥቶ ወደ ስራ ተገብቷል ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
እንደ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ገለጻ ህብረተሰቡ ግብይቶችን በሚያካሂድበት ጊዜ ከአጭበርባሪዎች እና ከህገ-ወጦች ያልተገባ ድርጊት ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል።
የቁም እንስሳትን በሚገበያዩበት ጊዜ የብር ኖቶችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን (በሞባይል ባንኪነግን) ሲጠቀሙ የብሩን መጠን በማረጋገጥ እና ወደ አካውንታቸው መግባቱን በደምብ ማስተዋል ይጠበቃል ብለዋል።
ለምግብነት በሚውሉ ልዩ ልዩ ግብዓቶች ላይ በዓድ ነገራትን ቀላቅለው የሚሸጡም ሊኖሩ ስለሚችሉ በጥንቃቄ መገበያየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር የዕሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በአሉን ለማክበር ወደ ወዳጅ ዘመድ በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ ያልተገባ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ የተቀናጀ የቁጥጥር ስራ እየተካሄደ እንደሆነም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ በመግለጫቸው አብራርተዋል።
ትርፍ በሚጭኑ የትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉም አክለዋል።
ለዚህም ስኬት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ዜጎች ያለ አንዳች እንግልት እንዲንቀሳቀሱ እና በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ የተለያዩ የወንጀል እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት እና በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ወቅት ችግር ሲገጥመው ለጸጥታ አካላት በመጠቆም የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ቀጣይ በሪፎርም ስራዎቻችን የተገኘውን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የምንሰራበት ዓመት ይሆናል ሲሉ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ለመላው የአማራ ክልል ህዝብ፣ ለመከላከያ እና ለፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም ለመላው የጸጥታ ኃይል ለ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት በራሴ እና በዋና ጠቅላይ መምሪያው ስም እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

