የፖሊስ መታወቂያን ጨምሮ ሌሎች ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት ወንጀል ሲፈፅም የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 14 ነዋሪ ከሆነው ያረጋል ጥላሁን ከተባለ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ልዩ ልዩ ማህተሞችና ቲተሮችን በመጠቀም ሀሰተኛ ሰነዶችን እንደሚያዘጋጅ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መረጃ እና ክትትል መምሪያ ከባህርዳር ከተማ ፖሊስ ጋር በጋራ በጥናት ላይ የተመሠረተ መረጃ በማሰባሰብ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ገልጿል።
በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ ሀሰተኛ የፖሊስ መታወቂያን ጨምሮ በርካታ የተዘጋጁ እና ሊዘጋጁ የተሰናዱ ሀሰተኛ ሰነዶችን እንዲሁም ግለሰቡ ሀሰተኛ ሰነዶቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀምባቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችም ተይዘዋል፡፡
በተጠርጣሪው ላይ አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
ተቋማት ግለሰቦች አገልግሎት ፈልገው በሚመጡበት ወቅት የሰነዱን ትክክለኛነት ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ማረጋገጥ እንደሚገባም ፖሊስ አሳስቧል።
ሀሰተኛ ሰነዶች የፍትህ ስርዓቱን በማዛባት እንዲሁም ለበርካታ ወንጀሎች መከሰት መንስኤ እንደሚሆኑ በመረዳት ከድርጊቱ እንዲታቀቡ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስገንዝቧል።
መሰል ወንጀሎች እየተበራከቱ መሆኑን የገለፀው ፖሊስ ኅብረተሰቡ ወንጀሉን በመፀየፍ የድርጊቱን ፈፃሚዎች ሲያገኝና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለፖሊስ መረጃ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።







