“የፀጥታ ኃይላችን የፅናት ተምሳሌት ናቸው። ፅናት ደግሞ የፀጥታ ኃይላችን መገለጫ ነው” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
ጳጉሜን 1 የፅናት ቀን ‘ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር’ በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል።
አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ መንገሻ ፈንታሁን (ዶ/ር) የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በስነ-ስርዓቱ ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን አክብሯል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ፅናት የሰራዊት ሁለንተናዊ ማሳያ ነው ብለዋል።
የክልለችን የፀጥታ መዋቅር ከፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆና ለዘመናት የከፈሉት ተጋድሎ የፅናት ትልቁ ማሳያ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ፖሊስም የጀመረውን የሪፎርም ስራ እና ወደ ከፍታ ዘመን የመንደርደር ጉዞ የበለጠ ለማጠናከር አበክረን እንሰራለን ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ተናግረዋል።
የተጀመረውን ሪፎርም ውጤታማ በማድረግ ህዝባችን ከገጠመው የፀጥታ ችግር እንዲወጣ ጸንተን በጋራ መረባረብ ይገባናል በማለት አሳስበዋል።
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የፅናት ቀንን ስናከብር የሀገርን ክብርና የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በዱር በገደሉ እስከ ህይወት መስዕዋትነት ዋጋ የከፈሉ እና እየከፈሉ የሚገኙ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎችን በማሰብ ነው ብለዋል።
“የፀጥታ ኃይላችን የፅናት ተምሳሌት ናቸው። ፅናት ደግሞ የፀጥታ ኃይላችን መገለጫ ነው” ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የፅናት ቀን ስናከብር ሀገራችን የጀመረችውን የእድገት ጉዞ ለማስቀጠል እንዲሁም የተከፈለን መስዕዋትነትን ለመዘከር እና የሀገርን ደኅንነት ለማስቀጠል ፀንተን መቆማችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የዘመናት የትግልና የፅናት ትልቅ ማሳያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፍፃሜ ብስራትም ሌላው የፀጥታ ኃይሉ የፅናት ማሳያ ነው ሲሉ ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት የፅናት ቀንን ባከበርንበት ማግስት መሆኑ ትልቅ ደስታና ተስፋን ያሰነቀን መሆኑን ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የፅናት ቀን ሲከበር አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
የጳጉሜን 1 የፅናት ቀን ‘ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር’ በሚል መሪ ቃል በሀገር ዓቀፍ ደረጃ እና በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
ፅናት የሰራዊት መገለጫ በመሆኑ ከሰራዊት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው መሆኑም ተገልጿል።












