የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአመራር ምደባ አካሄደ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአመራር ምደባ አካሄደ

‎የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለዋና ክፍል ኃላፊዎች ምደባ ተሰጥቷል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ ከሪፎርም በፊት ግልጽ የሆነ የምደባ ስርዓት አለመኖሩን አንስተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ እያካሄደ ካለው ሪፎም ወዲህ ምደባዎች ግልጽ እና ስታንዳርድን የተከተለ በመሆኑ ፖሊስ በስራ አፈጻጸም ብቃታቸው እና በስነ-ምግባራቸው ማደግ እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የገለጹት።

የፖሊስ ስራ ፈታኝ እና ውስብስብ በመሆኑ የተሰጣችሁን ሙያዊ ኃላፊነት በተገቢው መንገድ ልትወጡ ይገባል ብለዋል።

ተቋማዊ አሰራርን እና አንድነታችን አጠናክረን ህዝብን ማገልገል ይጠበቅብናል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ።

በተሰጠን ኃላፊነት ልክ በማገልገል የአማራን ህዝብ ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ እንደሚገባም በዋና ጠቅላይ መምሪያው የዋና ክፍል ኃላፊነት ምደባው ወቅት ምክትል ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

በምደባው የከፍተኛ መኮንኖች ሲሆን የትምህርት ደረጃን፣ የስራ አፈጻጸምን እና ስነ-ምግባርን መሰረት አድርጎ ጾታን ያማከለ ነው ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሩ አክለው ተናግረዋል።

የኃላፊነት ምደባ ለተሰጣቸው ከፍተኛ መኮንኖች ህገመንግስቱ እና ህግን እንዲሁም ለህሊናችሁ ታማኝ በመሆን ሰራዊቱን እንዲመሩ እና ህዝብን እንዲያገለግሉ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የኃላፊነት ምደባና የማዕረግ እድገት አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱን ተከትሎ መስጠቱ የሪፎርሙ አንዱ ውጤት በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር መላኩ ሲሳይ የዋና ጠቅላይ መምሪያው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።

ምደባ የተሰጣቸው ከወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ፣ ከወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ፣ ከአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁም ለኮሚሽነሩ ተጠሪ ከሆኑ ዋና መምሪያዎች እና መምሪያዎች መሆኑን የዋና ጠቅላይ መምሪያው የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አብዮት ሽፈራው ገልጸዋል።

በስነ-ስርዓቱ የታደሙት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ የዋና ክፍል ኃላፊዎች ምደባ ሙያ እና ሙያተኛን ያገናኘ በመሆኑ ለቀጣይ ስራዎች መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግርዋል።

ዋና ክፍል ኃላፊ ሆነው የተመደቡ መኮንኖች ህዝብን በቅንነት በማገልገል የተጣለብንን ተቋማዊ እና ህዝባዊ ኃላፊነት የሚመጥን ስራን መከወን ይገባናል ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

በዋና ክፍል ኃላፊነት የተመደቡ አመራሮች በቅንነት፣ በታማኝነት እና ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተከትለው ማህበረሰቡን ለማገልገል ቃለ-መሀላ ፈጽመዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top