ከተማዋ የተረጋጋች እና ሰላማዊ እንድትሆን የሰራዊቱ ተጋድሎ እና የህዝብ አጋርነት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተገለጸ።
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ያለው ዘለቀ ከተማዋን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ የፖሊስ ኃይሉ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የፖሊስ ሰራዊቱ ህዝብ አጋር በማድረግ በወንጀል መከላከል፣ በህግ ማስከበር እንዲሁም ልዩ ልዩ ሁነቶች በሰላም እንዲከበሩ በማድረግ ደብረ ታቦር ከተማ አሁን ላለችበት ሰላም ጉልህ ሚና ማበርከቱ ነው ኮማንደር ያለው የገለጹት።
ደብረ ታቦር ከተማ ፖሊስ ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን ከከተማዋ ዙሪያ በደፈጣ ስራ ላይ ተሰማርቶ በህገ-ወጥ ቡድኖች ላይ ርምጃ በመውሰድ አንፀባራቂ ድሎችን አስመዝግቧል።
የፖሊስ ኃይሉ ከክልሉ አድማ መከላከል፣ ከሚሊሻ፣ ከሰላም አስከባሪ እንዲሁም ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን የከተማዋን ሰላም ሊሚያውኩ የሚሞክሩ አካላትን ለመመከት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ነው ኮማንደር ያለው የተናገሩት
በወንጀል መከላከል፣ በትራፊክ ቁጥጥር እና በወንጀል ምርመራ ተግባራት በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል ብለዋል።
ዋና ኢንስፔክተር አግማስ ጌቴ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ኬላዎችን ዘርግተው የፍተሻ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ኢንስፔክተር አግማስ ገለጻ በኬላ ፍተሻው በህግ የሚፈለጉ ወንጀለኞች፣ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾች እንዲሁም የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች ተይዘዋል።
የቤት ለቤት ፍተሻ፣ የአከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ እዲሁም የብሎክ አደረጃጀቶችን በመፍጠር የወንጀል መከላከል ተግባራትን እያከናወን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
በደብረታቦር ከተማ ሲካሄድ የነበረው የደብረታቦር (የቡሄ) በዓል በሰላም መጠናቀቁን ኮማንደር ያለው ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።













