“በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የአማራ ክልል ፖሊስ በቂ ዝግጅት አድርጓል።” ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ

“በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የአማራ ክልል ፖሊስ በቂ ዝግጅት አድርጓል።” ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ

በአማራ ክልል የሚከበሩ ሐይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ነሐሴ 13 የቡሄ በዓል እንዲሁም ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 21 ድረስ በአማራ ክልል የሚከበሩ በዓላት ናቸው።

ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በክልሉ የሚከበሩ ሐይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ በቂ ዝግጅት መደረጉን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የጸጥታ ኃይሉ ስነ-ምግባርን ተላብሶ ህግ እንዲያስከብር ዝርዝር ዕቅድ ታቅዶ በየደረጃው ከሚገኙ አመራር እና አባላት ጋር ውይይት ተካሂዶበት ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

በክልሉ በሚከወኑ በዓላት ዙሪያ በዝርዝር ዕቅዶች ላይ ከህዝብ ጋር ሰፊ ውይይት መካሄዱንም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ሰላም ወዳዱ የአማራ ህዝብ ህገ-ወጥ ቡድኖችን አውግዞ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት አየሰራ አንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ከሌሎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ እና የደኅንነት አካላት ጋር በጥምረት አየሰራ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በዓሉ በሚከበርባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ እና ቋሚ ጥበቃ መመደቡን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ ህዝቡ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ስጋት ሊያከብር ይገባል ብለዋል።

ህዝቡ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለጸጥታ ኀይሎች መጠቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

ከቅድመ መከላከል አልፎ ወንጀሎች ከተፈፀሙ በተፋጠነ የህግ ስርዓት ውሳኔ ለማሰጠት የሚያስችል የምርመራ ቡድን መዋቀሩንም ምክትል ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።

በዓላትን ስናከብር በመከባበር መሆን እንደሚገባ የጠቆሙት የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ ለአረጋውያን፣ ለሴቶች እና ለህፃናት አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top