“የአማራ ክልል ፖሊስ ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሪፎርም እያካሄደ ነው” ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለዞን እና ለከተማ አሰተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዦች እና ምክትል አዛዦች ምደባ አካሂዷል።
ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጊዜያዊ የሰው ኃይል ምደባ መመሪያ እና ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ነው የኃላፊነት ምደባው እየተካሄደ የሚገኘው ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ሁለንተናዊ ሪፎርም እያካሄደ መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ኮሚሽነሩ በሰው ኃይል እና በተቋም ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሪፎርም እያካሄደ ነው ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር፣ የአሰራር ስርዓት እና አደረጃጀት በመዘርጋት እንዲሁም የሰው ኃይሉን አቅም በማጎልበት የአገልግሎት አሰጣጡን ፍትሐዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ምክትል ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ ለስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ለዞን እና ለከተማ አሰተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዦች ስልጠና ተሰጥቶ ምደባው ተካሂዷል።
የዋና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም የዞን እና የከተማ አሰተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዦች እና ምክትል አዛዦች ምደባ ተጠናቋል ብለዋል።
የዋና ጠቅላይ መምሪያው እና የዞን ዋና ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም የወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት እና የፖሊስ ጣቢያ አዛዦች ምደባ በቀጠይ የሚካሄድ ሲሆን እስከ ባለሙያ ምደባ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።
ማዕረግን፣ የትምህርት ዝግጅትን፣ ስነ-ምግባርን እና አቅምን መሰረት አድርጎ የተካሄደ ምደባ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ አስታውቀዋል።

