በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለከፍተኛ መኮንኖች ማዕረግ እድገት ተሰጥቷል
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማዕረግ ሽግግር ያደረጉ ለከፍተኛ እና ለመስመራዊ መኮንኖችን የማዕረግ እድገት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት አካሂዷል።
በስነ-ስርዓቱ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ እንደተናገሩት ማዕረግ ትልቅ ዋጋና ድካምን የሚሻ እንዲሁም የዓመታት የልፋት ውጤት በመሆኑ ትልቅ ክብር አለው ብለዋል።
የልፋትና የጥረት ውጤት የሆነውን ማዕረግ ለመቀበልም እንደ ከዚህ ቀደሙ በዘፈቀደ ሳይሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በክብርና ስርዓቱን ጠብቆ መሆኑ ተገቢ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ በዛሬው ዕለት የማዕረግ ዕድገት ያገኛችሁ ከፍተኛ መኮንኖች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ኮማንደር አብዮት ሽፈራው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰው ኃብት አስተዳደር እና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው በበዛሬው ዕለት 14 መኮንኖች ወደ ኮማንደር፣1 ወደ ምክትል ኮማንደር፣ 8 ወደ ዋና ኢንስፔክተር እንዲሁም 2 የኢንስፔክተር ማዕረግ ያገኙ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህ ታላቅ ክብር በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ማዕረግ ማንኛውም አካል በዘፈቀደ የሚያገኘው ሳይሆን የብዙ ድካም እና ትጋት ውጤት መሆኑን የገለጹት የማዕረግ እድገት ያገኙ መኮንኖች ማዕረግ ሲሰጥ ከከባድ የህዝብ ኃላፊነት ጋር በመሆኑ ለማዕረጉና ለሙያው የሚመጥን ተግባር መወጣት ይገባናል ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለማዕረግ ልዩ ትኩረት እና ክብር በመስጠት የማዕረግ እድገት አሰጣጡ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከናወን ማድረጉ የሚበረታታ እና የሚመሰገን ተግባር ነው ሲሉ አብራርተዋል።















