ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋና መልካም አገልግሎት ለመስጠት የስራ ቦታን ምቹ ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው አሰራር መሆኑ ተገለጸ።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ከፍተኛ የፌዴራል የስራ ኃላፊዎች በባህርዳር አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ማርች ባንድ እና የክብር ዘብ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህንጻ ዕድሳት እና የማስፋፊያ ስራዎች የምረቃ ፕሮግራም በኋላ የክልሉን ፖሊስ የለውጥ ስራዎችን እና አዲስ የቢሮ ማስፋፊያ ግንባታዎችን ጎብኝተዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማስፋፊያ እና አዲስ የቢሮ ግንባታን በጎበኙበት ወቅት አንደገለጹት “ለማኀበረሰቡ ቀልጣፋና መልካም አገልግሎት ለመስጠት የሰራተኛውን የስራ ቦታ ምቹ ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው አሰራር ነው” ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው በፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያው የተፈጠረው ምቹ የስራ ቦታ እና የግንባታ ሂደቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ፖሊስ እያካሄደ ላለው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደማይለየው ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ የአማራ ክልል ፖሊስ ተቋምን በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት ያስፈለገው ‘ኅብረተሰቡን ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ ለማገልገል ነው’ ብለዋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም አዲሱን የቢሮ ግንባታ እና የማስፋፊያ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ቀን እና ሌት ተግተን እንሰራለን ሲሉ በጉብኝቱ ለተገኙ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ለፖሊስ እያደረገ ላለው ድጋፍ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ምስጋና አቅርበዋል።











