“የፖሊስ ተቋምን በማዘመን እና ሪፎርሙን ውጤታማ በማድረግ የአማራ ክልልን ህዝብ ሰላም እናረጋግጣለን” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ2017 የበጀት ዓመቱን የስራ አፈፃፀምን እና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል።
ከወቅቱ የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ እና ደኅንነት አካላት ጋር በቅንጅት በተሰሩ የህግ ማስከበር ስራዎች በርካታ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት መቻሉ በአመታዊ ሪፖርቱ ተገልጿል።
የክልሉ አድማ መከላከል ፖሊስ የተለያዩ የእጀባ ስራዎችን መስራቱ በበጀት ዓመቱ ከተተገበሩ ጠንካራ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም ተነስቷል።
በትራፊክ ቁጥጥር ስራን በማጠናከር ለመንገድ ትራንስፖርት ፍሰቱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር መቻሉም በዓመታዊ ሪፖርቱ ተመላክቷል።
በበጀት ዓመቱ በአራት ቀጠናዎች የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ ከፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን ከክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ 171 መዝገቦችን አጣርቶ በማደራጀት ለሚመለከተው የፍትሕ ተቋም በመላክ አብዛኞቹ ውሳኔ መሰጠቱ በሪፖርቱ በጥንካሬ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
የአመራር ምደባ ብቃትን መሰረት ያደረገ መሆኑ፣ የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያው ቀጥታ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተጠሪ መሆኑ፣ ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖር ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅን ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ማሳደግ እና መሰል ስራዎች በጥንካሬ ከተነሱ ተግባራት መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በበጀት አመቱ የስራ አፈጻጸም ውይይት ላይ እንደገለጹት “የፖሊስ ተቋምን በማዘመን እና ሪፎርሙን ውጤታማ በማድረግ የአማራ ክልልን ህዝብ ሰላም እናረጋግጣለን” ብለዋል።
በደም እና በአጥንት ህዝባችንን የሚያገለግል የፖሊስ ሰራዊት ባለበት በዚህ ወቅት ከፖሊስ ስነ-ምግባር ዉጭ የሚደረጉ ማናቸዉመ ጉዳይ ተቀባይነት የላቸዉም።
የፖሊስ ተቋም የማህበረሰቡ ተግባሩን በሰላም እንዲከውን ማስቻል እና ወንጀልን መከላከል ነው ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም ይህን ተቋም የሚመጥን ተግባር በመፈጸም የተጣለብንን ኃላፊነት መወጣት ይገባል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ መደበኛና የኦፕሬሽን ስራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቦባቸዋል፤ ይሁን እንጂ ከወቅቱ የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከዕቅድ አንፃር የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውንም ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ያነሱት።
የሰራዊቱን አቅም ማሳደግ፣ የህዝብ ግንኙነት ስራን ማጠናከር፣ የአባላት አያያዝን ማሻሻል፣ ፖሊሳዊ ስነ-ስርዓት እና የዕዝ ሰንሰለት እንዲከበር ማድረግ፣ በሰራዊቱ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ሊፈታ የሚችል አሰራርን መፍጠር የሚሉ አንኳር ጉዳዮች በ2018 በጀት ዓመት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በትኩረት የሚሰራባቸው መሆኑን ኮሚሽነር ዘላለም አስታውቀዋል።
















