የአማራ ክልልን የጸጥታ ችግር በራስ አቅም ለመፍታት እየተደረገ ያለው ስራ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበበት መሆኑ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ፣ የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ፣ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ተጠሪ የሆኑ ዋና መምሪያዎች እና መምሪያዎች የበጀት ዓመቱን የስራ አፈጻጸማቸውን አስመልክቶ ግምገማ አካሂዷዋል።
ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ የአማራ ክልልን የጸጥታ ችግር በራስ አቅም ለመፍታት እየተደረገ ያለው ስራ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑ ከባለፋት ዓመት አንፃር በጥንካሬ የሚወሰድ ተግባር ነው ብለዋል።
ከወቅቱ የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ እና ደኅንነት አካላት ጋር በቅንጅት በተሰሩ የህግ ማስከበር ስራዎች በርካታ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት ተችሏል ብለዋል።
የክልሉ አድማ መከላከል ፖሊስ የተለያዩ የእጀባ ስራዎችን መስራቱ በበጀት ዓመቱ ከተተገበሩ ጠንካራ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የገለጹት።
የእገታ ወንጀል የፈጸሙ ከ1 ሺህ በላይ ወንጀለኞች ተይዘው ህጋዊ እርምጃ እነደተወሰደባቸው የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያው ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል።
ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ በ2017 ዓ.ም ከተከናወኑ ተጨባጭ ተግባራት መካከል የፖሊስ ኃይሉን ለማጠናከር እስከ ወረዳ ድረስ የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።
በመደበኛ እና አድማ መከላከል ፖሊስ የሚስተዋሉ የሰው ኃይል እጥረቶችን ለመፍታት በአዲስ ምልመላዎች ተደርገው ስልጠና በመስጠት የክልሉን ጸጥታ እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሰው ኃይል የማጠናከር ስራ መሰራቱን ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅን ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት እንዲያድግ የተደረገው ተግባር በበጀት ዓመቱ ከተከወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በበጀት ዓመቱ በአራት ቀጠናዎች የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ ከፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን ከክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ 171 መዝገቦችን አጣርቶ በማደራጀት ለሚመለከተው የፍትሕ ተቋም በመላክ አብዛኞቹ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል።
በባህርዳር፣ በጎንደር እና በደብረ ብርሃን በህገወጥ መንገድ በተደራጁ የቤት ማህበራት ስም ሊመዘበር የነበረ የከተማ ቦታዎች ወደ መንግስት እንዲመለሱ ተደርጓል።
በተለያዩ ከተሞች የፍንዳታ ማቴርያሎችን በመጠቀም የሽብር ተግባር የፈጸሙ እና ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ህገ-ወጥ ቡድኖችን ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ በግምገማው አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ተጠሪ የሆኑ የኮሚሽነሩ ልዩ ጽሕፈት ቤት፣ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ፣ የወንጀል ክትትል እና መረጃ ዋና መምሪያ እና ሌሎች መምሪያዎች አመታዊ የስራ አፈጻጸማቸውን ገምግመዋል።
የክልሉ ፖሊስ ሰራዊቱ ከሌሎች የፌደራል የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በርካታ ፀረ-ሰላም ቡድኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ ወስዷል፤ ቀላልና ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እና ተተኳሽ ጥይቶች መማረካቸውም ተገልጿል።
ሀገራዊና ክልላዊ ሁነቶች በክልሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ የወንጀል ክትትል እና መረጃ ዋና መምሪያው ተግባሩን መከወኑ ነው በግምገማው የተነገረው።
ህዝብና ፖሊስን እንደ ድልድይ ሆኖ በማገናኘት እና በማቀራረብ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ተግባሩን በብቃት መወጣቱን የዋና መምሪያው ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ተናግረዋል።
የፖሊስን ተግባሮች እና መረጃዎችን ወቅቱን ጠብቀው ለህዝቡ እና ለሰራዊቱ በማድረስ በኩል የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያው ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ውጤት እየተመዘገበባቸው በመሆኑ እስከ ወረዳ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በአመታዊ የየጠቅላይ መምሪያዎች ግምገማ ላይ በተወያዮቹ ተጠቁሟል።














