የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር የጸጥታ ምክር ቤት ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አስተላለፈ።
የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር ከዚህ በፊት የከተማችንን የጸጥታ ኹኔታ መነሻ በማድረግ የኅብረተሰቡን ደህንንነት ከማስጠበቅ አኳያ ልዩ ልዩ ክልከላዎችን የጸጥታ ምክር ቤቱ ማውጣቱ ይታወቃል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በባሕርዳር ከተማ አስተዳድር በተከታታይ በተሠራው ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ እና በኅብረተሰቡ የላቀ ተሳትፎ የከተማዋ የሰላምና የጸጥታ ኹኔታ በከፍተኛ ኹኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ምክር ቤቱ ገምግሟል።
የከተማው ፀጥታ ምክር ቤት ሌላው አፅዕኖት ሰጦ የተመለከተው የከተማው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኹኔታ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ መሆኑንና ይህንኑ በላቀ ኹኔታ ለማሳለጥና የከተማችን የቱሪዝም እና የልማት ተግባራት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚከተሉትን ከዚህ በፊት ተጥለው የነበሩ ክልከላዎችን በከፊል አንስቷል ። ከእነዚህም መካከል፦
1. ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ያለገደብ 24 ሰዓት ክፍት በማድረግ እንዲሠሩ ተወስኗል፣
2. ከባጃጅ እና ከሞተር ሳይክል ውጭ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ ተወስኗል፣
3. ማንኛውም ሰው ያለምንም የሰዓት ገደብ እንዲንቀሳቀስ ተፈቅዷል፣
ማሻሻያ ያልተደረገባቸውና አሁንም የተጣሉ ግዴታዎችን በተመለከተ፦
1.ማንኛውም ተሽከርካሪ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የፊት ለፊትና የኋላ ሰሌዳ አሟልቶ መንቀሳቀስ አለበት ይህንን ሳያደርግ ተገኝቶ በጸጥታ ሀይሉ ለሚወሰደው ማንኛውም ሕጋዊ እርምጃ ኅላፊነቱን ራሱ ይወስዳል፣
2.ማንኛውም እግረኛ ሲንቀሳቀስ ማንነቱን የሚገልጽ የቀበሌ የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ መገኘት አለበት፣
3.የጸጥታ ሀይሉ እና በሚኖሩበት ቀበሌ ወይም ቀጠና ወይም ብሎክ ብቻ መሳሪያ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ከፈቀደላቸው መሳሪያ ፈቃድ ኩፖን ከተሰጣቸው ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በፍጹም የተከለከለ ነው፣
4.የባጃጅ ተሽከርካሪ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት በኋላ ይዞ መንቀሳቀስ ክልክል ነው፣
5.ባለ ሁለት እግር ሞተር በማንኛውም ሁኔታ ይዞ መንቀሳቀስ በፍጹም የተከለከለ መኾኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ገጽ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

