“ብዙ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሩም ፈተናው በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቋል” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሲሰጥ የቆየው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በሰላም ተጠናቋል ብለዋል።
ብዙ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሩም ፈተናው በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ኃይሉ ተግባሩን በባለቤትነት ይዞ በጥብቅ ዲስፕሊን መመራቱን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
መተባበር፣ መቀናጀት፣ መናበብና ነገን አስበን በእልህና ቁጭት መስራት ከቻልን የማንሻገረው ፈተና የማንፈታው ችግር አይኖርም ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም ያሳለፍናቸው ሁለት አመታት በሁሉም ተግባራትና የፈተና ስራው ያስተማሩንና ያስተዋልነው መልካም ተሞክሮ ይህንን ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በሂደቱ የተሳተፉ አካላት መልካም እና ቅን ትብብር ታክሎበት ለዚህ ውጤት በቅተናል።
ለፈተናው ሂደት አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ጠንቅቃችሁ የሰራችሁ፣ በፈተና ሂደቱ የተሳተፋችሁ ሁሉም አካላት በእኔና በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ከእድሜያቸው በላይ አስበው እና ተጨንቀው ላሳዩት መልካም ስነ-ምግባር ያመሰገኑት ኮሚሽነሩ መልካም እድል እንዲገጥማቸውም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በየደረጃው ያላችሁ የትምህርት ቤተሰቦች ክልላችን የገጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን አሁን ያለንን መተባበር የበለጠ በማጠናከር ህዝባችንን ከጎናችን አድርገን የትውልድን ቅብብሎሽ በጥራትና በፍትሃዊነት እንድናስቀጥል አደራየን አቀርባለሁ ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም ተናግረዋል።

