ለ34ኛ ዙር የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ምልምል ፖሊስ ሰልጣኞች የስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄደ
ለ34ኛ ዙር የአማራ ክልል ፖሊስ የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ምልምል ሰልጣኝ ፖሊሶች በብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ትምህርት ቤት የስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ወታደራዊ አዛዦች፣ የዩኒቨርስቲ ኮሌጁ የማኔጀመንት አባላት፣ መምህራን እና አሰልጣኞች ተገኝተዋል።
በስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሸነር አበበ ደለለ እንደገለፁት ሰልጣኝ ምልምል ፖሊሶች በወቅታዊ ሁኔታውና በሀሰተኛ ወሬ ሳትደናገሩ የፖሊስ ሙያን ወዳችሁ እና መርጣችሁ ስለመጣችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ረዳት ኮሚሽነሩ አክለውም የዚህን ዙር ስልጠና ለየት የሚያደርገው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ያደገበት እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሪፎርም እያካሄደ ባለበት ወቅት ስለሚሰጥ የተሻለ ሞራልና መነቃቃት ይፈጥራል በማለት ተናገረዋል።
በክልላችን ያጋጠመውን የሠላም መደፍረስ በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ የእናንተ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በመምህራን እና በአሰልጣኞች የሚሰጣችሁን ስልጠና በተገቢው መንገድ መከታተል ይጠበቅባችኋል ሲሉ ለምልምል ሰልጣኝ ፖሊሶች አስገንዝበዋል።
የስልጠናው ዋና አሰተባባሪ ኮማንደር ግዛቸው ከበደ በበኩላቸው ሰልጣኞች በትምህርትም ሆነ በአካል ብቃት ብቁ እንዲሆኑ መምህራን እና አሰልጣኞች የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል።
ሰልጣኞችም የሚሰጣቸውን ስልጠና በወኔ እና በተነሳሽነት በመሰልጠን የአማራን ህዝብ በፖሊስነት ሙያ ለማገልገል ጉጉት እንዳደረባቸው መግለጻቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የህዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቋል።






