“የፖሊስን የከፍታ ዘመን ማሳያ ምልክቶች ናችሁ” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ
በአብክመ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የስነ-ስርዓት ቁጥጥር እና የክብር ዘብ ስልጠና የወሰዱ ሰልጣኝ ፖሊሶችን አስመርቋል።
በዕለቱ የተገኙት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ እንደተናገሩት ፖሊስን ፖሊስ ሊያሰኙ የሚችሉ ፖሊሳዊ ስነ-ስርዓትን አንግባችሁ የፖሊስ የመጭው የከፍታ ዘመን ማሳያ ምልክቶች ናችሁ” ብለዋል።
የስነ-ስርዓትና ቁጥጥር ዋና ክፍሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ለጀመረው የከፍታ እና የለውጥ ጉዞ አይነተኛ ሚናን ይወጣል ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም ፖሊስን በአለባበሱና ወታደራዊ ስርዓቱ ከሌሎች ሲቪሎች እንዲለይ የሚያደርገውን ባህሪ የምታንፀባርቁ ናችሁ።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም ገለጻ የአማራ ክልል ፖሊስን ወደ ከፍታ ለማድረስ በፖሊሳዊ ስነ-ምግባር የታነጸ፣ ስነ-ስርዓትን አክብሮ የሚሰራ የፖሊስ ሰራዊት እየተገነባ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ፖሊሳዊ ተግባራትን ለማከናወን ከሚተገበሩ የሪፎርም ስራዎች መካከል አንዱ ወታደራዊ ስነ-ስርዓትን አክብሮ መንቀሳቀስ ነው ይህንንም ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ ነው ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በመለዮው እና በማዕረጉ የሚኮራ የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባትም አይነተኛ ሚና አላችሁ ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም የዋና ጠቅላይ መምሪያው አመራርም ሆነ አባል የደንብ ልብስ አሟልቶ እና ስነ-ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
በቀጣይም በሁሉም አካባቢ ባሉ የፖሊስ ጣቢያዎች የፖሊሳዊ ስነ-ስርዓት ቁጥጥሩ ተግባራዊ ይሆናል ሲሉም ኮሚሽነር ዘላለም አሳስበዋል።









