በክረምት ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል እየሰሩ መሆኑን ኮማንደር በቀለ አብዬ ተናገሩ
በክረምት ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ በአብክመ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር በቀለ አብዬ ተናግረዋል።
የትራፊክ አደጋ ከወትሮው በተለየ መልኩ በክረምት ወቅት ይጨምራል ያሉት ኮማንደር በቀለ ችግሩን ለመከላከል በክልል ደረጃ አገልግሎት የማይሰጡ የመንገድ ላይ የትራፊክ ምልክቶች እና ማመልከቻዎች እየተስተካከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የትራፊክ ተቆጣጣሪ ፖሊሶች እና የመንገድ ትራንስፖርት ባለሙያዎች ለአሽከርካሪዎች እና ለእግረኞች የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ኮማንደር በቀለ አብራርተዋል።
የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመከላከል ከወንጀል መከላከል ክፍሎች እና ከክልሉ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በቅንጅት እና በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዋና መምሪያ ኃላፊው ተናግርዋል።
በክረምት ወቅት መንገዶች በዝናብና ጭጋግ ስለሚሸፈኑ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች የትራፊክን ህግና ደንብ በማክበር እንዲሁም በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ ይኖሮባቸዋል ሲሉም ኮማንደር በቀለ አብዬ መልዕክት አስተላልፈዋል።

