ከኅብረተሰቡ ጋር የተሻለ ቅንጅት በመፍጠር የጸጥታ ስራውን በውጤታማነት መፈፀም እንደሚገባ ተገለጸ
የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ የ100 ቀናት የጸጥታ ስራ አፈፃፀም ግምገማ በፍኖተሰላም ከተማ አካሂዷል።
በግምገማው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ የቅድመ ወንጀል መከላከል ስራውን በማጠናከር የህዝቡን ደኅንነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ ከኅብረተሰቡ ጋር የተሻለ ቅንጅት በመፍጠር የጸጥታ ስራውን በውጤታማነት መፈፀም ይገባል።
ጠንካራ የምርመራ ተግባራትን በማከናወን የህግ የበላይነትን ለማስከበር በትኩረት መስራት ይጠበቃል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ምቹ ለማድረግ የቁጥጥር እና የክትትል ስራን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ኮማንደር በሪሁን አየነው የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው የፖሊስ ሰራዊቱ የመፈፀም አቅሙን በማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የፀጥታ ሁኔታውን ለማረጋጋት የኅብረተሰቡን ሰላም የሚነሱ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል አስፈላጊ ምርመራ በማድረግ ተገቢ የሆነ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
ከህግ ማስከበር ስራው ጎን ለጎን መደበኛ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስራም በትኩረት እየተሰራ መኾኑን አብራርተዋል።











