የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የረጅም ጊዜ አገልግሎት ሸልማት እና የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የፖሊስ ሰራዊት የማዕረግ ዕድገት ሰጠ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተለያዩ መረሐ-ግብሮችን አካሂዷል።
ህዝብን ማገልገል ክብር ነው በሚል መሪ ቃል
በተካሄደው መርሐ-ግብር በፖሊሰ ተቋም የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሠጡ የፖሊሰ አባላት እና አመራሮች የአገልግሎት ሸልማት ተሰጥቷል።
በተቋሙ የአገልግሎት ጊዜያቸውን የሸፈኑ በሙያዊ ክህሎትና ስነ-ምግባር የተሻሉ፣ የስራ አፈፃፀማቸው አጥጋቢና ከዚያ በላይ ላስመዘገቡ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት የማዕረግ ዕድገት የተሰጠ ሲሆን ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመትና በላይ ላገለገሉ የሰራዊት አባላት በየ ደረጃው የወርቅ፣ የብር፣ የነሀስ ሜዳይ እና የሪቫን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ኮሚሸነር እና የአስተዳደር ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ለረጅም ጊዜ ለማዕረግ ክብር የማይሰጥበት ብሎም ማዕረግ እንደ ትክሻ ምልክት ይታይ የነበረበት ጊዜ አልፏል ብለዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ አሁን ላይ ማዕረግ በፖሊስ ሰራዊቱም ሆነ በሕዝብ ልዩ ክብር እና ትርጉም ያለዉ በመሆኑ በተሰጣቸሁ የአገልግሎት ዘመን ሸልማትም ሆነ የማዕረግ እድገት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንዲሁም ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል ኃላፊነታችሁን በብቃት እንድትወጡ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተሰጣችሁ የማዕረግ እድገት እና የአገልግሎት ዘመን ሽልማት ለዓመታት ያለፋችሁበት የፖሊስነት ሙያ በሰጣችሁ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት ይህን እድል ወደ ተግባር ለመቀየር ተጨማሪ ብርታትና የላቀ ኃላፊነት በመሸከም ለአዲስ የተሻለ ውጤትም ያተጋችኋል ያሉት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር መላኩ ሲሳይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ልዩ ጽሕፈት ቤት ዋና መምሪያ ኃላፊ ናቸው።
ኮማንደር አብዮት ሽፈራው የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኀላፊ በበኩላቸው ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር፣ በሳል አመራር እና ሕዝባዊ መሠረት ወሳኝ መሆናቸዉን ተናግረዋል።
የተሰጣችሁ የአገልግሎት ዘመን ሽልማት እና የማዕረግ እድገት ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት መሆኑን በመገንዘብ እንኳን ደሰ አላችሁ ወደፊትም ለተሻለ ስኬት መነሳሳት ይገባችኋል ሲሉ ኮማንደር አብዮት ሽፈራው አሳስበዋል።












