“በአማራ ክልል ሙያዊ ስነምግባርንና ብቃትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ ፖሊስ የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች ምደባ ተከናውኗል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በምደባው ወቅት እንደገለጹት “በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሙያዊ ስነምግባርንና ብቃትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ ፖሊስ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል”
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሪፎርም ዋና አላማው ፖሊስን ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለስ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ዘላለም አሁን ላይ በተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም ገለጻ የተቋም አቅም የሚገነባው በአሰራር ነው፤ ምደባው ችሎታን፣ አቅምን እና ብቃትን መሰረት በማድረግ የተከናወነ በመሆኑ አንዳችን የአንዳችን ጉድለት በመሙላት ለህዝብ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ይጠበቃል።
የተሰጣችሁ ኃላፊነት የህዝባችንን ሰላም እና ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም የአማራ ክልል ህዝብን ለማገልገል ነው የሚል እስቤ ይዛችሁ የተጣለባችሁን ህዝባዊ ኃላፊነት እስከ ህይወት መስዕዋትነት በመክፈል ጭምር ሊሆን እንደሚገባ ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው ገልፀዋል ።
ከጊዜው እና ከዓለም ጋር እኩል የሚራመድ፣ የሚያነብ እና ራሱን የሚያበቃ የፖሊስ አመራር መሆን ይጠበቅባችኋል።
የአማራ ክልል ህዝብ ቁርጠኛ የፖሊስ አመራር በሚፈልግበት ወቅት የተመደባችሁ የስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በመሆናቸው ቀን እና ሌት በመስራት የህዝቡን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የፖሊስ አገልግሎት ከሌብነትነ እና ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት የሚሰጥ፣ በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የማይገባ፣ ከሐይማኖት ወገንተኝነት የራቀ እንዲሁም ከከባቢነት የፀዳ ሊሆን ይገባል ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም አዲስ ለተመደቡ የስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች አጽንኦት በመስጠት አብራርተዋል።
በአዲስ ከተመደቡ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ኮማንደር ራሄል አብርሃም እና ምክትል ኮማንደር መሰለ ስዩም ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የለውጥ ሂደት በማጠናከር ህዝብ የሚፈልገውን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው እርብርብ የድርሻችን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።









