በቅድመ ጥንቃቄ ጉድለት ሊከሰት የሚችልን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ስልጠና ተሰጠ።
በምዕራብ ጎጃም ዞን በግዳጅ ቀጠና ለተሰማሩ 602ኛ ኮር የሀገር መከላከያ ሰራዊት አሽከርካሪዎች በቅድመ ጥንቃቄ ጉድለት ሊከሰት የሚችልን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷል።
ሌተናል ኮሎኔል ግርማ መንግስቱ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የ602ኛ ኮር የትራንስፖርት ኃላፊ እንደገለፁት ስልጠናው የሀገር መከላከያ ሹፌሮች በግዳጅ ወቅትም ይሁን በማንኛውም ሰዓት በሚያሽከረክሩበት ጊዜ በጥንቃቄ ጉድለት ሊከሰት የሚችልን አደጋ መቀነስ ያስችላል ብለዋል።
አደጋ እንዳይከሰት የተሰጠው ስልጠና ከዚህ በፊት የነበራቸውን ዕውቀት የሚያጠናክር እና አዳዲስ የትራፊክ ደንቦችን አውቀው እንዲያሽከረክሩ የሚያግዝ ስልጠና መሆኑን ሌተናል ኮሎኔል ግርማ ገልጸዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር አዱኛ ሙሉ የተሰጠው ስልጠና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሹፌሮች በሚያሽከረክሩበት ወቅት በሰው እና በንብረትላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ቀድሞ ለመጠንቀቅ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
ኮማንደር አዱኛ አክለውም በምዕራብ ጎጃም ዞን የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ለአሽከርካሪዎች እና ለማህበረሰቡ ስለ ትራፊክ ህግና ደንብ ስልጠና መስጠታቸውን ተናግረዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ሻለቃ ባሻ በግዱ ጉተማ እና ፲ አለቃ ፀጋ ሞላ እንደተናገሩት የነበራችውን ዕውቀትና ልምድ ያጠናከረ እንዲሁም የትራፊክ ደንቦችን ጠንቅቀው አውቀው በማሽከርከር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚያደርግ ስልጠና ማግኘታቸውን ተናግረዋል።





