በሰዎች መነገድና ደንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የስራ እድል ፈጠራ ላይ ማተኮር ይገባል ተባለ።

በሰዎች መነገድና ደንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የስራ እድል ፈጠራ ላይ ማተኮር ይገባል ተባለ።

በሰዎች ላይ መነገድ፣በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀሎች በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱና ለሰብአዊ መብት ጥሰት እያጋለጡ ይገኛል።

በተለይ በሀገራችን በተደጋጋሚ በተከሰቱ አለመረጋጋቶች ምክንያት በቂ የስራ እድል አለመፈጠሩ በርካታ ዜጎቻችን በህግ ወጥ መንገድ ለስደት በመዳረጋቸው ስቃይ እና መከራ እየደረሰባቸው መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው።

የአማራ ክልል ደግሞ ለዚህ ወንጀል መነሻና መተላለፊያ ሆኗል። በ2017 በጀት ዓመት በአማራ ክልል የተፈጸሙ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች 402 ሲሆኑ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ድንበር አቋርጠው ለመሰደድ በህገወጥ መንገድ ሲጓዙ በፖሊስ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ይህንን ህገወጥ ተግባር እየፈጸሙ የሚገኙ 126 ደላሎችም በቁጥጥር ስር ውለው ተገቢው የምርመራ ስራ መከናወኑን የፖሊስ ሪፖርት ያመለክታል።

እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ለማስተግበር ከፍተኛ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን በመከላከል በኩል ኃላፊነት ያለባቸው የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ፣ የክልሉ ፍትህ ቢሮና የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚመለከታቸው አካላት ወንጀሉን በጋራ መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄደዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌዉ በፍትህ ተቋማት መካከል የሚታየው አለመናበብ ለወንጀል ፈጻሚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተው በተለይ በምርመራ ማጣራትና ለፍትህ በማቅረብ ሂደት የሚታዩ መጓተቶች ወንጀሉን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት በዚህ የወንጀል ሂደት ውስጥ እጃቸው መኖሩ ጉዳዩን ውስብስብ እንዳደረገው ያነሱት ም/ኮሚሽነር ታደሰ አያሌዉ በዚህ ሂደት ውስጥም በበጀት ዓመቱ 215 የወንጀል መዝገቦችን ማጣራት መቻሉን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም በበኩላቸው ክልሉ የወንጀሉ መነሻ እና መዳረሻ በመሆኑ ይሄን ለመከላከል የድርጊቱን መተላለፊያና መነሻ ላይ ትኩረት ያደረገ የፍትህ ስርዓትን መተግበር ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ የዜጎችን የስራ እድል ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት ውጤታማ አለመሆንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የስራ አጥነት ቁጥር ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል እንደ ዋና መንስኤ መሆኑን ገልፀው መንግስት የውጭ አገር የስራ ስምሪትን በህጋዊ መንገድ ለማሰማራት የሚያደርገው ጥረት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ አለመሆን ችግሩ እንዲባባስ ትልቅ አስተዋጾ አበርክቷል ብለዋል።

ይህንን ለመቅረፍ የወቅቱ የፀጥታ መደፍረስ ችግር ቢሆንም የዜጎችን የስራ ክህሎት በማሳደግ ከሀገር እስከ ሀገር ውጭ የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በልዩ ትኩረት በጋራ ትብብር ሊሰራ የሚገባው መሆኑን አንስተው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top