“የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚከናወኑ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ
የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት የጥምር የፀጥታ ኃይሉ በተለይ የክልሉ ፖሊስ የተለያዩ የሰላም ጥበቃ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ፖሊስ ወደ ነበረ ከፍታውና ዝናው እንዲመለስ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የገለፁት ክብር ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ፖሊሱ በከፍተኛ መነሳሳት የህብረተሰቡን የሰላምና ደህንነት ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከሰላም ወዳድ ህብረተሰብ ጋር በመሆን በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ ያነሱት ኮሚሽነሩ የትውልዱን ተስፋ ለመንጥቅ ያሰፈሰፍ የጥፋት ሀይሎችን በቅንጅት መከላከል ይገባል ብለዋል።
ከብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናው በተጨማሪ ሌሎች በክልሉ የሚከወኑ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተከናውኗል ያሉት አዛዡ የፀጥታ ኃይሉ ለሰላም ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ተግባር እንዲወጣም አሳስበዋል።

