ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አካሄደ
የፌደራል፣ የክልሎች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች በወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ እና በ26ኛው ዙር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ምልመላ ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት ነው ያካሄዱት።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የሀገራችን የፀጥታ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እየተለወጠ ነው፤ ቀጣይም ሀገራችን የሚመጥን የፀጥታ ስምሪት በማካሄድ ኢትዮጵያ ሙሉ አቅሟን በልማት ላይ እንድታውል ሁሉም የፀጥታ አካላት ትኩረት ሰጥተው መረባረብ ይገባል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር እና በባለቤትነት እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ጀነራሉ ሰላም እና ፀጥታን በማስከበር የወንጀል ስጋቶችንም እየተከላከሉ ነው ብለዋል።
የፀረ-ሰላም ኃይሎችን እኩይ ተግባር በማክሸፍ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙም ጨምረው አብራርተዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገለጻ በአራቱም የሀገራችን ማዕዘናት ፍተሻዎችን በማጠናከር ሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የጦር መሣሪያ፣ የማዕድንና የአደገኛ ዕፅ ዝውውርን እንዲሁም የኮንትሮባንድ እና ሌሎች መሰል የወንጀል እንቅስቀሴዎችን በቅንጅት መከላከል ይገባል ሲሉ በውይይቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የፖሊስ ተቋም የፀጥታ ስምሪት በማድረግ እና የትራፊክ ደኀንነትን በማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና መወጣት እንዳለባቸው ኮሚሽነር ጀነራሉ ገልፀዋል፡፡
“Leadership Challenges” በሚል ርዕስ ላይ በማተኮር ክልሎችን ያሳተፈ ስልጠና ለመስጠት በጋራ እንደሚሠራ ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሪፎርም ሥራዎች የደረሰበትን የቴክኖሎጂ አቅም ወደ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተቋማት ለማስፋት በጋራ እና በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የ26ኛ ዙር መሠረታዊ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምልመላ ዕቅድ ዙሪያ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ምልመላው ከአሁን በፊት ከነበረ በተሻለ ሁኔታ የብሔር ብሔረሰቦችን እና የፆታን ተዋፅኦ ባገናዘበ መልኩ መከናወን እንዳለበት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የሥራ መመሪያ መስጠታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።









