“የአማራ ክልል ፖሊስ ወደ ቀድሞ ከፍታው እና ዝናው መመለስ አለበት” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በምስራቅ አማራ በመገኘት ከዞን፣ ከሜትሮፖሊታን፣ ከሪጅዮፖሊታን ከተማዎች እና ከፖሊስ ጣቢያ አዛዦች እና አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ እንደገለጹት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያደረገ ያለው ሪፎርም በአገልግሎት አሰጣጡ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት በስነ-ልቦና ልዕልና እና በሞራል ከፍታ የሚነሳበት ዘመን መሆኑን አብራርተዋል።
የፖሊስ ሰራዊቱ ጓዳዊ ትስስሩን በማጎልበ፤ በአዛዥ እና ታዛዥ መካከል ያለውን ወታደራዊ የዕዝ ሰንሰለት ጠብቆ ህዝብን ማገልገል ይገባል።
“የአማራ ክልል ፖሊስ ወደ ቀድሞው ከፍተው እና ዝናው መመለስ አለበት” ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በጀግንነት እና በሃላፊነት ስሜት የተጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም ምንጊዜም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ይጠበቃል ሲሉም ለሰራዊቱ አስገንዝበዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም ገለጻ የአገልግሎት አሰጣጣችን ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለው እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ታማኝነትን የሚያጎለብት መሆን አለበት።
ፖሊስ ለህዝብ እና ለመንግስት ቃል በገባነው መሰረት ለሰንደቁ ፍቅር እና ለመለዮው ክብር በታማኝነት እና በጀብደኝነት ተልዕኮን መፈፀም ይገባል።
የህዝቡን የሰላም ጥማት ለማርካት ከመቸው ጊዜ በላይ በትጋት በመስራት እጅ ለእጅ ተያይዘን እና በጋራ ፀንተን መቆም ይገባናል ሲሉም ኮሚሽነሩ በአፅንኦት አስረድተዋል።
ፖሊስ ዘመኑን የዋጀ፣ በእውቀት እና በቴክኖሎጂ የላቀ እንዲሆን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያካሄደ ያለው ሪፎርም አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ኮሚሽነር ዘላለም ገልጸዋል።
ፖሊስ ለህዝብ ጥቅም እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የገለጹት ኮሚሽነር ዘላለም በክልሉ የእተካሄደ ባለው ህግ የማስከበር ተግባር እና በተገኘው ውጤት ሳንኩራራ ለቀጣይ የኦፕሬሽን ተግባራት መዘጋጀት ይገባል ብለዋል።
መልካም ጅምሮች በማጠናከር እና የቀጣይ የስራ ዕቅዶችን በቀናነት በማከናወን የክልሉን ህዝብ ከገባበት የሰላም ማጣት ቅርቃር ውስጥ መንጥቆ ለማውጣት በሰብዓዊነት እና በጀግንነት መስራት ይገባል ሲሉም ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በምስራቅ አማራ ተገኝተው ለሰራዊቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በግንባታ ላይ ያሉ የፖሊስ ተቋማትን ጎብኝተዋል።







