“የሃይማኖት ተቋማት የሀገር ሰላም፣ የህዝብ አንድነት እና ልማት እንዲጠናከር የላቀ ሚና አላቸው” ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ሰላምና መቻቻል እንዲጎለብት የኃይማኖት ተቋማት የጀመሩትን አስተምህሮ እንዲያጠናክሩም ተጠይቋል።
“ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበርና ለአብሮነት” በሚል መሪ ሐሳብ 3ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የሰላም ጉባኤው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት የሃይማኖት ተቋማት የሀገር ሰላም፣ የህዝብ አንድነት እና ልማት እንዲጠናከር የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የግጭት መንስኤዎችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም እና ልማትን እውን ለማድረግ በውይይት መግባባት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የኃይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ በባህርዳር መካሄዱ ልዩ ትርጉም እንዳለው አንስተው በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ሰላምና መቻቻል እንዲጎለብት፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም የህዝብና የመንግስት ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን የሃይማኖት ተቋማት የጀመሩትን አስተምህሮ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ዋና ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመነጋገርና በውይይት መፍታት የሁሉም ግደታ መሆኑን አንስተዋል።
በ3ኛ የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤም በሀገራችን እንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ግጭቶችን በመነጋገርና በመመካከር ለመፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መሆኑን ገልጸዋል።
በኮንፈረንሱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
የሰላም ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት የሚኖረው ሚና የላቀ ነው መባሉን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።





