“የአማራ ክልል በውስጥም ሆነ በዙሪያው ያለው የሰላም ሁኔታ እየተለወጠ እና እየተቀየረ ነው” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ

“የአማራ ክልል በውስጥም ሆነ በዙሪያው ያለው የሰላም ሁኔታ እየተለወጠ እና እየተቀየረ ነው” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ

የጋራ ግብረ ኃይሉ ወቅታዊ የአማራ ክልልን የጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ግምገማ አካሄደ።

የአማራ ክልል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የአማራ ክልልን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታን አስመልክቶ ግምገማ አካሂዷል፡፡

በግምገማ መድረኩ የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታን የዳሰሰ ሰነድ ቀርቧል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ እንደገለጹት የጥምር ጦሩ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠናዎች ሁሉ ድልን እና ውጤትን በማስመዝገቡ አሁን ላይ አጠቃላይ በክልሉ ያለው ሰላም አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተወሰኑ ቆላማ ቀበሌዎች የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን በአጭር ጊዜ ለማጽዳት የጥምር ጦሩ በተቀናጀ እና በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉንም አንስተዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው እጅ ሰጥተዋል።

የክልሉ መንግስትም በሰላም እጅ ለሚሰጡ ታጣቂዎች በቂ የመቀበያ ቦታዎችን አዘጋጅቷል ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዘላለም ገለጻ የውሸት ጥምረት የፈጠሩ ህገወጥ ቡድኖች የአልሞት ባይ ተጋዳይ እንቅስቃሴያቸውን ለማድረግ በጠረፍ አካባቢ ካሉ የቅርብም የሩቅም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ሄደው የተላላኪነት እና የባንዳነት ተልዕኮ ይዘው መጥተው የአማራ ክልልን ሰላም ለማወክ የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር የጥምር ጦር ርምጃ በመውሰድ እያከሸፈባቸው ይገኛል።

የህገወጥ ቡድኖች የሽብር ድርጊት እንዳይሳካ በማድረግ በኩል የክልሉ ህዝብ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል የሚሉት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በዚህም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚካሄዱ ሁነቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር ተከናውነዋል እየተከናወኑም ይገኛሉ ብለዋል።

አሁን ላይ በክልሉ እየተገኘ ላለው ሰላም የፀጥታና ደህንነት ተቋማቱ በትብብር የመስራት ውጤት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በክልሉ በሚገኝበት ጠረፍ አካባቢዎች ያሉ ትንኮሳዎች ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ በማድረግ እና በመቀልበስ በኩል የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌደራል የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

አጠቃላይ የአማራ ክልል ሰላም በውስጥም ሆነ በዙሪያው ያለው ሁኔታ እየተለወጠ እና እየተቀየረ ያለበት ሂደት መሆኑንም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በክልሉ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ግምገማ ላይ አብራርተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top