“ለህዝብ ሲል ራሱን ለመስጠት የማይሰስት፣ ሁኔታዎችን እና ፈተናዎችን ያለፈ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነው የፖሊስ ኀይል ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር በህግ ማስከበር ዙሪያ ትልቅ ዋጋ ከፍሏል” ኮማንደር ቢምረው አሰፋ
ኮማንደር ቢምረው አሰፋ የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ አንደገለጹት ጥምር ጦር አባላት የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ እና ወንጀልን ለመከላከል ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ለህዝብ ሲል ራሱን ለመስጠት የማይሰስት፣ ሁኔታዎችን እና ፈተናዎችን ያለፈ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነ የፖሊስ ኀይል ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር በህግ ማስከበር ዙሪያ ትልቅ ዋጋ ከፍሏል ብለዋል።
እንደ ኮማንደር ቢምረው ገለጻ ፖሊስ በከተማዋ እየተፈፀሙ ያሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል እና ህግን ለማስከበር ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን እየተገበረ ይገኛል።
በመደበኛ እና በአድማ መከላከል ፖሊስ፣ በሚሊሻ፣ በሰላም አስከባሪ እና በሌሎች የፀጥታ አካላት ጥምረት
የታጠቁ ህገ-ወጥ ቡድኖችን በመፋለም እና ስርዓት በማስያዝ ለደብረ ማርቆስ ከተማ እና አካባቢዋ ሰላም መስፈን ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
አሁን ያለውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባራትን እየፈጸምን እንገኛለን የሚሉት የፖሊስ አዛዡ ህገ-ወጦችን ወደ ፍትህ አደባባይ ለማምጣትም የተጠና እና የተጠናከረ የኦፕሬሽን ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
ባለፉት 11 ወራት ከ215 በላይ የክስ መዝገቦች ተጣርተው ለሚመለከተው የፍት አካል እንዲላኩ መደረጉን ኮማንደር ቢምረው ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ሚሊሻ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንሙት ገላነህ በበኩላቸው የክልሉ ጥምር ጦር ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ለከተማዋ አሁናዊ ሰላም እንደ ሻማ እየቀለጠ፣ እንደ ፀሀይ የበራ ኀይል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፖሊስ ሰራዊት እና ሚሊሻ ለጋራ አላማ በጋራ የሚተጋ ሰራዊት ነው ያሉት ኃላፊው ለከተማችን አሁናዊ ሰላም ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን የከፈለው ዋጋም አኩሪ ገድል ነው ብለዋል።
የደብረማርቆስ ከተማን ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም አካል ሊረባረብ ይገባል የሚሉት የጸጥታ አመራሩ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበል ይገባል ሲሉም ለታጠቁ ቡድኖች ጥሪ አቅርበዋል።




